ባለስድስት ስሙ "አውቆ አበድ" ወንጀለኛ ፀያፍ የማምለጫ ሙከራው ከተጠያቂነት አልታደጉትም
ግለሰቡ ጤና እንደራቀው ለማሳየት በላዩ ላይ እስከመፀዳዳት ቢደርስም ፓሊስ ባደረገው ክትትል ተደርሶበታል
የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ከ1990 ጀምሮ 16 ወንጀሎችን ፈፅሟል የተባለውን ግለሰብ ከወንጀል ተጠያቂነት የማምለጥ ሙከራ በማህበራዊ ትስስር ገፁ አጋርቷል
በአዲስ አበባ ሰርቆ እጅ ከፍንጅ ሲያዝ "ማበዱን" ያወጀው ግለሰብ የረቀቀ የማምለጫ ዘዴው ተደርሶበት በእስራት መቀጣቱን የመዲናዋ ፓሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
ጌቱ ከበደ እና ጌቱ ነጋሽ በሚል የተለያዩ ስሞች የሚጠቀመው ግለሰብ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ሉባር ሆቴል ተብሎ ቢጠራው አካባቢ በአንድ የመኖሪያ ቤት ውስጥ ገብቶ 19 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ አልባሳትን ሰርቆ ሲወጣ በአካባቢው ነዋሪዎች እጅ ከፍንጅ ሲያዝ "ዕብደቱ" እንደጀመረው ፓሊስ ይገልፃል።
ወዲያውኑ ራሱን የሳተ መስሎ መሬት ላይ ተጠቅልሎ የተኛው ጌቱ፥ በአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ ፖሊስ በስፍራው ሲደርስም "አልናገር፤ አልጋገር" ማለቱን ኮሚሽኑ ያወሳል።
ግለሰቡ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተወስዶ በተደረገ ምርመራም ግለሰቡ የጤና ችግር እንደሌለበት ቢረጋገጥም ማስመሰሉን ገፋበት የሚለው ፓሊስ፥ ነገሮች ባሉበት ሁኔታ መቀጠላቸው ጥርጣሬ መፍጠሩን ይገልፃል።
ግለሰቡ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ስድስት የተለያዩ ስሞችን እየተጠቀመ 16 የተለያዩ ወንጀሎችን መፈፀሙ ከፌደራል ፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራ የተገኘው የጣት አሻራ ሪከርድ ማመላከቱም ጥርጣሬውን አጎላው።
የአዕምሮ ችግር ይኖርበት ከሆነ በሚልም ከአቃቤ ህግ ጋር በመነጋገር የወንጀሉን ጉዳይ እየተመለከተ የሚገኘው ፍርድ ቤት ለአማኑኤል የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታል ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው መጠየቃቸውን ያነሳል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን።
የጤና ምርመራው እየቀጠለ ፖሊስ ክትትሉን በሚያጠናክርበት ወቅት ጌቱ ከበደ ወይም ጌቱ ነጋሽ ለ3 ወራት ያህል ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው ፖሊስ ተሸክሞት ነበር፡፡
"ቀን ቀን መፀዳጃ ቤትም አይሄድም፡፡ ምሽት ላይ ደግሞ እዚያው ማረፊያ ክፍል ውስጥ ይፀዳዳል" የሚለው ፖሊስ መሰል ከተጠያቂነት የማምለጫ ዘዴዎች አዲስ ስላልነበሩ በድብቅ መከታተል ጀመርኩ ይላል።
ፖሊስ ምግብ ሲያቀርብለት የማይበላው፤ ጭር ሲልለት ደግሞ የቀረበለትን የማያስተርፈው ጌቱ፥ ፖሊስ ሲያየው መተኛትን ከአጠገቡ ሲርቁ ደግሞ ተነስቶ መቀመጥን ሁነኛ የማምለጫ ዘዴው አርጎ ገፋበት።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የፖሊስ አባላት በሞባይል ስልካቸው በድብቅ ይቀርፁት ነበር ያለው ኮሚሽኑ፥ የ3 ወራቱ የፖሊስ ጣቢያ ቆይታው ከተጠናቀቀ በኋላ ፍርድ ቤቱ በማረሚያ ቤት ቆይቶ ጉዳዩን እንዲከታተል ይወስናል።
ፖሊስም ተጠርጣሪውን ለማረሚያ ቤት ወስዶ ሲያስረክብ ማረሚያ ቤቱ "በሸክም የመጣ ተጠርጣሪ አንቀበልም" ብሎ እንደመለሰው ፖሊስ ያወሳል።
ይህንኑ ፍርድ ቤት ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ በመስጠቱ የጤንነቱን ሁኔታ የሚያረጋግጥ የህክምና ማስረጃ እስኪመጣ ድረስ በማረሚያ ቤት ውስጥ ለ 1 ዓመት ያህል መቆየቱ ተመላክቷል።
ከአማኑኤል ሆስፒታል የመጣው የምርመራ ውጤት ግን ጌቱ ከበደ ወይም ጌቱ ነጋሽ ምንም አይነት የአዕምሮ ህመም የሌለበት መሆኑን ማሳየቱን የሚጠቅሰው የአዲስ አበባፖሊስ ኮሚሽን፥
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዲስ ከተማ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በቅርቡ በዋለው ችሎት ጥፋተኛ ብሎት በአምስት አመት እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል ብሏል።
የፓሊስ ከአንድ አመት በላይ የዘለቀ ትዕግስት የተሞላበት ምርመራ "አውቆ አበዱን" ወንጀለኛ ተጠያቂ ማድረግ መቻሉንም አድንቋል።