በሴኔጋል ነፍሰጡር የፓርላማ አባልን በጥፊ የመታው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ
በታህሳስ ወር የፓርላማው ብጥብጥ ተሳትፎ ያደረገ ሌላ የምክር ቤት አባልም በስድስት ወራት እስራት መቀጣቱ ተነግሯል
በሴኔጋል ፓርላማ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የታየው ብጥብጥ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረትን ስቦ እንደነበር ይታወሳል
የሴኔጋልን ፓርላማ ወደ ብጥብጥ ማዕከልነት የለወጡት የምክር ቤት አባላት በስድስት ወራት እስራት ተቀጥተዋል።
ነፍሰጡር የምክር ቤት አባልን በጥፊ የመታውና በግርግሩ ተሳትፎ አድርጓል የተባለው የፓርላማ አባልም ተመሳሳይ ቅጣት ተላልፎበታል።
ማሳታ ሳምብ የተባሉት የምክር ቤት አባል የበጀት ጉዳይ ምክክር ሲደረግ ሃሳቤን ባልተገባ መንገድ ተቃውማለች ያሏትን ኤሚ ዲየ ጂኒቢ በጥፊ መምታታቸው ምክር ቤቱን ብጥብጥ ውስጥ ማስገባቱ ይታወሳል።
በጥፊ የተመቱት ጂኒቢ ወደ ሳምባ ወንበር ሲወረውሩም፥ አማዱ ኒያንግ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል ሆዳቸውን በእርግጫ መቷቸዋል።
ለያዥ ለጋናዥ አስቸጋሪ የነበሩት የምክር ቤት አባላት ድርጊት በቀጥታ በቴሌቪዥን መተላለፉም በሴኔጋል ቁጣ ቀስቅሶ እንደነበር ስካይ ኒውስ አስታውሷል።
በዳካር የሚገኘው ፍርድ ቤትም በሁለቱ የምክር ቤት አባላት ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰዱ ነው የተነገረው።
ከስድስት ወራት እስራቱ ባሻገር 8 ሺህ 144 ዶላር ካሳን ለጂኒቢ እንዲከፍሉ ተወስኗል።
ቅጣት የተላለፈባቸው የምክር ቤት አባላት የተቃዋሚው ፒ ዩ አር ፓርቲ አባላት ናቸው።
በጥፊ የተመቱት የነጂኒቢ ገዥው ጥምር ፓርቲ (ቤኖ ቦክ ያካር) ባለፈው ሐምሌ ወር በተካሄደው ምርጫ አብላጫ ድምጽ ማጣቱ የሚታወስ ነው።
ታህሳስ 1 2022 ላይ የተፈጠረው ብጥብጥም በሀገሪቱ በገዥው እና በተቃዋሚ ፖለቲከኞች መካከል ያለው በጠላትነት የመተያየት ስሜት እያደገ መምጣቱን ያሳየ ነው ተብሏል።
ገዥው ፓርቲ በሃምሌ ወሩ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ማጣቱን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በ2024 ለሶስተኛ ጊዜ ይወዳደራሉ ወይ የሚለውን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።
ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንቱ ከሁለት ጊዜ በላይ መወዳደር እንደማይችሉ እያነሱ ቢሆንም ማኪ ሳል እስካሁን ስለቀጣዩ አመት ምርጫ ተሳትፏቸው ያሉት ነገር የለም።