ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ወደ ቀድሞ የዲፕሎማሲ አቅሟ ትመለሳለች - የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር
ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የመከላከል ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት አድርጋ መቆየቷ ተገልጿል
ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ተከታይ በመሆኗ እንጂ የጎራ ልየታ አይደለም ተብሏል
ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ወደ ቀድሞ የዲፕሎማሲ አቅሟ እንደምትመለስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ በ2016 የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የትኩረት አቅጣጫዎች፣ የብሪክስ ጉዳይ እና ሌሎች ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ስራዎች ዙሪያ ትኩረት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ባለፉት ዓመታት በብዙ ምክንያቶች በመከላከል እና ማለዘብ ላይ ትኩረቱን ማድረጉን ነው አምባሳደር መለስ ያነሱት።
በ2016 በጀት ዓመት ግን የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ስራዎች ከማለዘብ እና ማስረዳት ባለፈ ወደ ወዳጅ ማብዛት እና ወደ ቀድሞ የዲፕሎማሲ መሪነት የሚመልሱ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ኢትዮጵያ በሀገራዊ፣ ክፍለ አህጉራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ተገቢውን ውክልና እና ተሳትፎ እንደምታደርግ ተናግረዋል።
እንዲሁም በላቲን አሜሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓ እና ሌሎችም አህጉራት ያሉ ለኢትዮጵያ ጥቅም ከሚያስገኙ ሀገራት ጋር ያለንን ዲፕሎማሲ ማጠንከር ላይ እናተኩራለን ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት የጠነከረ ወዳጅነት ከመሰረትንባቸው ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት እና ትብብር እንዲሰፋ ከማድረግ ባለፈ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ጥቅም ሊያስገኙልን ከሚችሉ እንደ አዛርባጂያን እና ቬትናም ያሉ ሀገራት ጋር ትብብራችንን እናጠናክራለን ብለዋል አምባሳደር መለስ ዓለም።
ኢትዮጵያ ብሪክስን ለምን መቀላቀል ፈለገች? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም "ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ተቋማትን በመመስረት ጥሩ ልምድ ያላት ሀገር ነች፤ ብሪክስም የዚህ አንድ አካል እንጂ የሆነን ቡድን ለመቃወም አልያም ለመደገፍ ብለን ያደረግነው አይደለም፤ ኢትዮጵያ ብዙ ፍላጎቶች እና ጥቅሞችን የምትፈልግ ሀገር ነች፤ ህዝብን ይጠቅማል፣ ተጨማሪ ትብብር እና ሀብት ለህዝባችን ይገኝበታል በሚል የተደረገ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን ተከትሎ በ17 የትብብር መስኮች ስምምነቶች መፈረማቸውን የተናገሩት አምባሳደር መለስ አብዛኞቹ ስምምነቶች የኢኮኖሚ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የፕሬዝዳንት ቢን ዛይድ የኢትዮጵያ ጉብኝት የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እና ኢትዮጵያ ግንኙነት ከተጠራጣሪነት ወደ መተማመን የሞላበት ወዳጅነት መቀየሩን እንደሚያሳይም አምባሳደር መለስ ተናግረዋል።