አሳታፊ ዓለም አቀፍ ሥርዓት እንዲኖር ኢትዮጵያ ከሁሉም ጋር ለመተባበር ዝግጁ ነች- ጠ/ሚ ዐቢይ
“የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያን በአባልነት መቀበሉ ለሀገራችን ታሪካዊ ሁነት ነው” ብለዋል
የብሪክስ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን እና አርጀንቲናን በአባልነት ተቀብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች ለሚሆን የበለፀገ የአለም ስርዓት መስፈን ከሁሉም ጋር ለመስራት ሁሌም ዝግጁ መሆኗን አስታወቁ።
በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ያለው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባዔ በዛሬው እለት አዳዲስ አባላትን ለመቀበል የወሰነ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ከተመረጡ ሀገራት መካከል አንዷ ነች።
ይህንን ተከትሎም በብሪክስ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ደቡብ አፍሪካ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻው ባስተላለፉት መልእክት፤ “የበሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ ሀገራችንን በአባልነት ተቀብሎ አፅድቋል፤ ይህ ለሀገራችን ታሪካዊ ሁነት ነው” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች ለሚሆን የበለፀገ የአለም ስርዓት መስፈን ከሁሉም ጋር ለመስራት ሁሌም ዝግጁ ናት” ሲሉም አስታውቀዋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን እና አርጀንቲናን በአባልነት መቀበላቸውን በዛሬው እለት በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሀገራቱ ብሪክስን መቀላቀል ብሪክስ በአለማቀፍ ደረጃ ተጽዕኖው ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ ነው ያስታወቁት።
የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በበኩላቸው፥ ውሳኔውን “ታሪካዊ ነው” ብለውታል።
ተጨማሪ ሀገራት ብሪክስን መቀላቀላቸው ለአለም ሰላም በጋራ ለመስራት ይበልጥ አቅም ይጨምራል ያሉት ደግሞ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ናቸው።
የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ደግሞ አዳዲሶቹ የብሪክስ አባል ሀገራት ብዝሃ ባህል ያላቸው መሆኑ የቡድኑን አካታችነት ያሳድጋል ነው ያሉት።
ኤምሬትስን ጨምሮ አዳዲሶቹ ብሪክስን እንዲቀላቀሉ የተመረጡት ሀገራት ከጥር 1 2024 ጀምሮ የቡድኑ አባል ይሆናሉ ተብሏል።
የዓለም የምጣኔ-ሀብት ታዳጊ ሀገራት የሆኑት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ በጋ የመሰረቱት ብሪክስ ስያሜውን ከአባል ሀገራት ስም በምህጻረ ቃል የወሰደ ሲሆን፤ በይፋ የተመሰረተው በጎርጎሮሳዊያኑ 2009 ነው።
ጥምረቱ በአሜሪካ እና በምዕራባውያን አጋሮቿ የሚመራውን የዓለምን ስርዓት ለመቃወም ለአባላቱ መድረክ ለመስጠት ተመስርቷል።
የቡድኑ መጠንሰስ የተጀመረው በሩሲያ ነው።