
በመተማመን እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተው ግንኙነታቸው በየጊዜው እያደገ ይገኛል
ኢትዮጵያ እና አረብ ኤምሬትስ በይፋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት በቀድሞው የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን የስልጣን ዘመን ነው።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፈረንጆቹ 2004 በኤምሬትስ የኢትዮጵያን ቆንስላ ከፍተዋል።
አረብ ኤምሬትስ ደግሞ በፈረንጆቹ 2010 በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን መክፈቷ የሚታወስ ነው።
የሁለቱ ሀገራት የቀድሞ መሪዎች በተለይ በ2014 በአቡ ዳቢ ባደረጉት ምክክር የሀገራቱን የንግድ እና ማህበራዊ ትስስር በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቀመጥ አድርገዋል።
የኤምሬትስ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት፣ በመከባበርና መተማመን ላይ የተመሰረተ ነው።
ይህም የሀገራቱን የሁለትዮሽና ቀጠናዊ ትብብር ያሳደገው ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በተለይ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሁለት አስርት ቅራኔያቸውን ፈተው ወደ እርቅ እንዲመጡ ኤምሬትስ የማሸማገሉን ሚና ተወጥታለች።
የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም “የዛይድ ሜዳል” በመሸለም እርቁ ጸንቶ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጀመር አበረታታለች።
ኢትዮጵጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ አለመግባባታቸውን በንግግር እንዲፈቱም ስታደርገው የቆየችውን ጥረት አሁንም ቀጥላለች።
አቡ ዳቢ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ በማድረግም የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ እየሰራች ነው።
ይህን የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ለማጎልበትም የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ አዲስ አበባ ገብተዋል።