በሲዳማ ክልል በመሬት መንሸራተት አደጋ የ6 ሰዎች ህይወት አለፈ
አደጋው ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ወንሾ ወረዳ ግሽሬ፤ጉዱሞና ሆሞ ተብሎ የሚጠራ አከባቢ ነው የደረሰው
በመሬት መንሸራተት አደጋ ከሞቱት በተጨማሪ በ6 ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል
በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ወንሾ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።
ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ወንሾ ወረዳ ግሽሬ፤ጉዱሞና ሆሞ ተብሎ የሚጠራ አከባቢ ትናንት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት መሬት በመንሸራተቱ የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የሲዳማ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።
በመሬት መንሸራተት አደጋ ከሞቱት በተጨማሪ ስድስት ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል ቢሮው በመግለጫው።
የክልሉ መንግሥት ከዞን አስተዳደር ጋር በመሆን አደጋ ከደረሰ ሰዓት አንስቶ በዜጎች ላይ ተጨማሪ አደጋ እንዳያደርስ የማድረጉ ስራና ተጎጂዎች ህክምና እንዲያገኙ አድርጓል።
የክልሉ መንግሥት ተጨማሪ ድጋፎዎችን ለማድረግ የክልሉ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና የፀጥታ ሀይል ወደ ስፍራው ማሰማራን አስታውቋል።
በሌሎች አከባቢዎችም መሰል ችግሮች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ማህበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የክልሉ መንግሥት የጥንቃቄ መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ250 ገደማ ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
በጎፋ ዞን የተከሰተውን የመሬት መንሸራትተ ተከትሎ አስከሬን የማፈላግ ስራው የቀጠለ ሲሆን፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለ የ3 ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን አውጇል።