ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በስፍራው ተገኝተው አፅናኑ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ጉዳት ወደ ደረሰበት ስፍራ አቅንተዋል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ3 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን አውጇል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በስፍራው ተገኝተው አፅናንተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዛሬው እለት በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ጉዳት ወደደረሰበት ስፍራ አቅንተው ስፍራውን ተመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደጋው ህይወታቸውን ባጡ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው ተጎጂዎችን ማጽናናታቸውን ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አደጋው መድረሱን ተከትሎ ከዚህ ቀደም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላፉት መልእክት፤ “በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ የበርካታ ዜጎቻችንን ሕይወት ቀጥፏል፤ በደረሰው አስከፊ ጉዳት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ” ብለዋል።
“አደጋውን ተከትሎ የፌዴራል የአደጋ መከላከል ግብረ-ሀይል በአካባቢው ተሰማርቶ የአደጋውን ጉዳት ለመቀነስ ርብርብ እያደረገ ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
በጎፋ ዞን በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የታወጀው ብሔራዊ የሀዘን ቀን ተጀምሯል
የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዛሬ ጀምሮ ቀጣይ ሶስት ቀናት ብሄራዊ የሃዘን ቀን እንዲሆን ማወጁን ተከትሎ ብሄራዊ የሀዘን ቀኑ ተጀምሯል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባሰለፍነው ሰኞ ጠዋት በደረሰ የመሬት መንሸራተተአደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 257 መድረሱን የተመድ እርዳታ ማስተባበርያ ቢሮ (ኦቻ ) አስታውቋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ኦቻ ትናንት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።