ኢትዮጵያ በ600 ሚሊየን ዶላር የነፋስ ሃይል ማመንጫ ለመገንባት ከኤምሬትስ ኩባንያ ጋር ተፈራረመች
300 ሜጋዋት የሚያመነጨው የንፋስ ሃይል ማመንጫ በሶማሌ ክልል አይሻ ነው የሚገነባው
ኢትዮጵያ እና አረብ ኤምሬትስ በታዳሽ ሃይል ልማት በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ
ኢትዮጵያ 600 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ልትገነባ ነው።
300 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል አይሻ በተባለ አካባቢ ነው የሚገነባው።
የኤምሬትሱ “ኤኤምኢኤ ፓወር” የንፋስ ሃይል ማመንጫውን ለመገንባት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
በኢትዮጵያ ግዙፉ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ይሆናል የተባለው ፕሮጀክቱ ለ2 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።
መቀመጫውን ዱባይ ያደረገው “ኤኤምኢኤ ፓወር” በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በርካታ የታዳሽ ሃይል ማመንጫዎችን ገንብቷል።
የአይሻ የንፋስ ሃይል ማመንጫም በመንግስትና በግል አልሚዎች ትብብር (ፒፒቲ) የሚገነባ ግዙፍ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ይሆናል ነው ያለው የገንዘብ ሚኒስቴር።
ኢትዮጵያ በአሰጎዳ እና አሰላ የንፋስ ሃይል ማመንጫዎች ከምታገኘው የኤሌክትሪክ ሃይል የላቀውን ከአይሻ ታገኛለች ተብሎም ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ እና አረብ ኤምሬትስ በታዳሽ ሃይል ልማት ትብብራቸው በየጊዜው እያደገ ይገኛል።
የኮፕ28 ጉባኤ በዱባይ ሲካሄድም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሀገራቸው በታዳሽ ሃይል ልማት ፈር ቀዳጅ የሆኑ ተግባራትን እየከወነች መሆኑን ማንሳታቸው አይዘነጋም።