የኢትዮጵያን ቀይ ባህርን የመጠቀም ፍላጎት ያሳካል የተባለ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን መንግስት ገለጸ
ሶማሊያ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የባህር በር ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል
ጽ/ፈት ቤቱ ስምምነቱ ወደ አዲስ የትብብር ማዕቀፍ የሚያስገባ እና ለአፍሪካ ቀንድ መስተጋብር የሚጠቅም ነው ብሏል
ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን የመጠቀም ፍላጎቷን ያሳካል የተባለ የመግባቢያ ሰነድ ከሶማሊላንድ ጋር መፈራረሟን መንግስት ገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን የመጠቀም ፍላጎቷን ለማሳካት መንገድ የሚጠርግ እና የወደብ አማራጮችን የሚያሰፋ የመግባቢያ ሰነድ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ላይ ተፈራርማለች።
ጽ/ፈት ቤቱ ሰነዱ ወደ አዲስ የትብብር ማዕቀፍ የሚያስገባ እና ለአፍሪካ ቀንድ መስተጋብር የሚጠቅም ብሏል።
በትናንትናው እለት የተወሰኑ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ወደብ በሊዝ ማግኘቷን የሚገልጽ ዘገባ አውጥተው ነበር።
ነገርግን ከቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ወደብ የምታገኝበትን ስምምነት ተፈራረመች በሚል ዘገባ ቀይረውታል።
የመግባቢያ ሰነዱ ይዘት የቀይ ባህር ወደብን መጠቀም ስለሚቻልበት ሁኔታ እንጅ ባለቤት መሆንን ወይ በሊዝ መግዛትን ማካተቱን የጽ/ቤቱ መግለጫ አልጠቀሰም።
ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በትናንትናው እለት ተፈራርመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት እና ጥያቄውን ለጎረቤት ሀገራት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተከትሎም ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ኤርትራ ጥያቄቀውን ውድቅ አድርገው ምላሽ ሰጥተውም ነበር፡፡
ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በብዙ ጉዳዮች ተባብራ እንደምትሰራ ገልጻ የቀይ ባህር ወደብ የመጠቀም ጥያቄን ግን እንደማትቀበለው አስታውቃለች፡፡
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አሊ ኡመር "የሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት- መሬት፣ ባህር እና አየር- ቅዱስ እና ለድርድር የማይቀርቡ ናቸው" ብላም ነበር፡፡
በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ መልስ አትስጥ እንጅ ኤርትራም በውሃ፣ የባህር በር በማግኘት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የሚሰሙ ንግግሮች እንዳልተመቿት ገልጻለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚሰሙ ንግግሮች መብዛታቸውን እና ግራ አጋቢ መሆናቸውን የገለጸችው ኤርትራ የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲጠነቀቁ አሳስባለች።
ጅቡቲም በተመሳሳይ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ውድቅ ያደረገች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ድጋሚ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ በሀይል የባህር በር ጥያቄዋን የመመለስ ፍላጎት እንደሌላት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡