ከዩክሬን ወደ ኢትዮጵያ የሚጓጓዝ እህል የምትጭን መርከብ ፒቭዴኒ ወደብ መድረሷ ተገለጸ
መርከቧ ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ እህል ለመጫን ያቀናች ነች
መርከቧ በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚላክ 23 ሺህ ቶን ስንዴ ትጭናለች
ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ የእህል ምርት የምትጭን መርከብ ወደብ ፒቭዴኒ ወደብ ላይ መድረሷን የዩክሬን የመሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቁ።
“ብሬቭ ኮማደር” የተባለችው መርከብ ፒቭዴኒ ወደብ ላይ መድረሷን እና በቅርቡም የዩክሬን የእህል ምርት ወደ ኢትዮጵያ የሚጫን መሆኑንም የዩክሬን የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ኦሌክሳንደር ኩብራኮቭ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
መርከቧ በጥቁር ባህር ላይ በሚገኘው ፒቭዴኒ በተባለ ወደብ ላይ መልህቋን የጣለች ሲሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከውን ስንዴ መጫን እንደምትጀምርም እየተጠበቀ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ በሰጡት አስተያየት፤ “ብሬቭ ኮማደር” የተባለችው መርከብ ስንዴ ጭና በምስራቅ አፍሪካ ወደምትገኘው ጅቡቲ የምታቀና መሆኑ እና ስንዴውም ጂቡቲ ወደብ ላይ ከተራገፈ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ይጓጓዛል ብለዋል።
ከዩክሬን የተጫነው ስንዴም የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች እያደረገው ላለው ኦፕሬሽን የሚውሉ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
መርከቧ 23 ሺህ ቶን ስንዴ ትጭናለች ተብሎ እንደሚጠበቅም የዩክሬን የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ኦሌክሳንደር ኩብራኮቭ አስታውቀዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በቱርክ አደራዳሪነት ምክንያት ዩክሬን ከወደቦቿ እህል ወደ ሌሎች ሀገራት እንድታጓጉዝ ከሩሲያ ጋር ከስምምነት መደረሱ ይተወሳል።
ስምምነቱን ተከትሎም ከቅርብ ቀናት ወዲህ በርካታ የጭነት መርከቦች የተለያየ መጠን ያለው እህል ከዩክሬን ወደቦች ላይ ጭነው መንቀሳቀሳቸው ይታወቃል።