ሶማሊያ የኢትዮጵያን የቀይ ባህር ወደብ የማግኘት ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ ተገለጸ
በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ መልስ አትስጥ እንጅ ኤርትራም የባህር በር በማግኘት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የሚሰሙ ንግግሮች እንዳልተመቿት ከትናንት በስትያ ገልጻለች
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል
ሶማሊያ የኢትዮጵያን የቀይ ባህር ወደብ የማግኘት ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ ተገለጸ።
ሶማሊያ የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበውን የቀይ ባህር ወደብ የመጠቀም ጥያቄ ውድቅ ማድረጓን ብሉምበርግ ዘግቧል።
- ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለመጠቀም እንደምትደራደር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ
- ስለባህር በር የሚደረጉ ንግግሮች ግራ አጋቢ እንደሆኑበት የኤርትራ መንግስት ገለጸ
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን እና ለመጠቀም ንግግር እንደሚያስፈልግ መግለጻቸው ይታወሳል።
እንደዘገባው ከሆነ ሶማሊያ በወደቦቿ ጉዳይ አትደራደርም።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አሊ ኡመር "የሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት- መሬት፣ ባህር እና አየር- ቅዱስ እና ለድርድር የማይቀርቡ ናቸው" ማለታቸውን ይኸው ዘገባ ጠቅሷል።
በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ መልስ አትስጥ እንጅ ኤርትራም በውሃ፣ የባህር በር በማግኘት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የሚሰሙ ንግግሮች እንዳልተመቿት ከትናንት በስትያ ገልጻለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚሰሙ ንግግሮች መብዛታቸውን እና ግራ አጋቢ መሆናቸውን የገለጸችው ኤርትራ የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲጠነቀቁ አሳስባለች።
ነገርግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር ተደርጎ የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ወደብ የመጠቀም ጉዳይ በጊዜ ካልተፈታ ቆይቶ ሊፈነዳ የሚችል የደህንነት ችግር እንደሚሆን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በ2030፣ 150 ሚሊዮን ይደርሳል፤ 150 ሚሊዮን ህዝብን ደግሞ "የጂኦግራፊ እስረኛ(ወደብ አልባ) ሆኖ መኖር አይችልም" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን በጉልበት ወይም በጦርነት መጋራት እንደሌለባት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በጦርነት እንዳይሆን ሀቅን መካድ" መቅረት እንዳለበት ተናግረዋል።
ስለቀይ ባህር ወደቦች ትኩረት አድርገው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በሶማሊያም ሆነ በጁቡቲ መተንፈሻ ወደብ እንደምትፈልግ ግልጽ አድርገዋል።
በቀይ ባህር ዙሪያ ያሉ ሀገራት በአባይ እና በተከዜ ጉዳይ ለመነጋገር ሳይፈሩ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት የራሷ ስለነበሩት ወደቦች መነጋገር መፍራት ተገቢ አይደለም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በምስራቃ አፍሪካ ቀጣና ካሉት ሀገራት ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ ወደብ ካጣች ከሶስት አስርት አመታት በላይ ሆኗታል።