3ኛው የላሙ ወደብ ስብሰባ በጁባ እንዲካሄድ ተወሰነ
የላሙ ወደብ ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር የተመረቀ ሲሆን፤ የመጀመሪያዋ መርከብም በእለቱ መልህቋን ጥላለች
የላሙ ወደብ የኢትዮጵያ፣ የኬንያ እና ደቡብ ሱዳን የጋራ ፕሮጀክት አካል ነው
ሶስተኛው የላሙ ወደብ የሚኒስትሮች ስብሰባ በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ እንዲካሄድ መወሰኑን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አስታወቁ።
አምባሳደር መለስ አለም የኢትዮጵያ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮች በኬንያ ሞምባሳ ባደረጉት ውይይት 3ኛው የላሙ ወደብ የሚኒስትሮች ስብሰባ ጁባ እንዲካሄድ መወሰኑን ገልጸዋል።
2ኛው የላሙ ወደብ ስብሰባ ሃምሌ 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን ቀጣዩ በደቡብ ሱዳን ይዘጋጃል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ፣ የኬንያ እና ደቡብ ሱዳን የጋራ ፕሮጀክት አካል የሆነው የላሙ ወደብ የመጀመሪያው የመርከብ ማቆያ በኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ሙይጋይ ኬንያታ ግንቦት 12 ቀን 2013 መመረቁ የሚታወስ ሲሆን የመጀመሪያዋ መርከብም በዕለቱ መልህቋን ጥላ ዕቃ አራግፋ ነበር።
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የላሙ ወደብ ግንባታ መከናወን ሶስቱን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በንግድ እና አገልግሎት ዘርፍ በማስተሳሰር የስራ ዕድል እንደሚፈጥር በወቅቱ ጠቅሰው ነበር።
ሌሎችም የፕሮጀክቱ አካላትም እንዲፋጠኑ የሥራ መመሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
በጊዜው በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ኢትዮጵያ ለላሙ ፕሮጀክቶች መሳካት አስፈላጊውን አስተዋፅኦ እንደምታደርግ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
የኬንያ መንግስት የላፕሴት ኮሪደር ልማት አካል የሆነውን የላሙ ወደብ ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት ሁኔታዎችን ሲያመቻች ቆይቷል።