ዩክሬን ለኢትዮጵያ የላከችው ስንዴ ጂቡቲ ወደብ መድረሱን ፕሬዝደንት ዜለንስኪ ገለጹ
ኬቭ በኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች 250 ሺህ ኩንታል ስንዴን ነው የምትልከው
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ “ምግብ ብቻ ሳይሆን ተስፋንም ልከናል” ብለዋል
ዩክሬን ለኢትዮጵያ የላከችው ስንዴ ጂቡቲ ወደብ መድረሱን የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ለኢትዮጵያ የሚሆን የእርዳታ ስንዴ የጫነችው መርከብ በጂቡቲ ዶራሌህ ወደብ ደርሳለች።
መርከቧ በሀገሪቱ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚከፋፈል 25 ሺህ ቶን ወይም 250 ሺህ ኩንታል ስንዴ መጫኗንም ነው የተናገሩት።
“ምግብ ብቻ ሳይሆን ተስፋንም ልከናል” የሚል መልዕክታቸውንም ስንዴ የጫነችው መርከብን ከሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ጋር አያይዘው ለጥፈዋል።
ዩክሬን በወደቦቿ የተከማቸ ስንዴን በድርቅና ረሃብ ለተጎዱተ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኮንጎ፣ ኬንያ እና የመን ለመላክ ከአጋሮቿ ጋር ስምምነት ተፈራርማለች።ኬቭ ወደሀገራቱ የምትልከው ስንዴ 150 ሚሊየን ዶላር እንደሚያወጣ ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ዜለንስኪም በቀጣዩ የፈረንጆቹ አመት መግቢያ ላይ ከ60 በላይ ስንዴ የጫኑ መርከቦችን ለተጎጂዎቹ ሀገራት እንልካለን ማለታቸውንም የሬውተርስ ዘገባ አመላክቷል።
ኬቭ ድጋፉን ወደ ሀገራቱ ለማድረስ ከ20 በላይ ሀገራት እና የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ አድርገውልኛል ብላለች።
በትናንትናው እለትም የቤልጂየም፣ ፖላንድ፣ ሊዩቲኒያ እና ሀንጋሪ መሪዎች የተሳተፉበት ጉባኤ በኬቭ ተካሂዷል።
የጀርመን እና ፈረንሳይ መሪዎችም በቪዲዮ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለየመን እና ሱዳን የእርዳታ ስንዴውን ለማድረስ የሚውል የ6 ነጥብ 24 ሚሊየን ዶላር ለመለገስ ቃል ገብተዋል።
የካቲት 24 2022 የጀመረው የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት የአለም አቀፉን የምግብ ዋስትና ተፈታትኗል።
ጦርነቱ አለም አቅፉ የግብርና ምርት አቅርቦት በ2021 ከነበረበት በ10 ሚሊየን ቶን እንዲቀንስ ማድረጉም በትናንቱ የኬቭ ጉባኤ ተነስቷል።
ይህም በበርካታ ሀገራት የምግብ ዋጋ ንረትን ማስከተሉ ተደጋግሞ ይገለጻል።
በጦርነቱ ምክንያት የተከማቸውን የዩክሬን ስንዴ በጥቁር ባህር በኩል ለአለም ገበያ ለማቅረብ በመንግስታቱ ድርጅት እና ቱርክ አደራዳሪነት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችም ፈተና ገጥሟቸዋል።
ለዚህም ሁለቱም ወገኖች ጣት የሚቀሳሰሩ ሲሆን፥ ሞስኮ የዩክሬን ስንዴ በድርቅ ለተጎዱ ሀገራት እየደረስ አይደለም የሚል ወቀሳን ታቀርባለች።
ኬቭ በበኩሏ ጂቡቲ የደረሰውን ለኢትዮጵያ የሚቀርብ ስንዴ ማሳያ አድርጋ ድጋፉ ለሌሎችም ሀገራት እንደሚቀጥል ገልጻለች።