ኢትዮጵያና የአቡዳቢው ‘ፊውቸር ኢነርጂ’ ኩባንያ የፀሀይ ኃይልን ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ
ኢትዮጵያ ለጸሐይ እና ነፋስ ታዳሽ ኃይል የሚሆን ሰፊ አቅም አላት- የማስዳር ዋና ሥራ አስፈጻሚ
ኢትዮጵያ ካላት ያልተነኩ አቅሞች ውስጥ የኢነርጂው ዘርፍ አንዱና ዋነኛው ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ
ኢትዮጵያና የአቡዳቢው ፊውቸር ኢነርጂ ኩባንያ 500 ሜጋ ዋት የፀሀይ ኃይልን በጋራ ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።
የፊርማ ስነ ስርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የማስዳር ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ ጃሜል አል ራማሂ በተገኙበት ነው በዛሬው እለት ተካሄደው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በስነ ስርዓቱ “ኢትዮጵያ ተከታታይ ሃገራዊ ለውጦች መካሄድ ከጀመሩበት ከ2010 ዓ/ም አንስቶ፣ በተለይም የግሉን ዘርፍ መዋዕለ ነዋይ በመጠቀም ኢኮኖሚዋን ለማጠናከር ስትሠራ” መቆየቷን ተናግረዋል።
ዶ/ር ዐቢይ “ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በበርካታ ዘርፎች ያልተነካ አቅም አላት ያሉም ሲሆን፣ እንደዚህ አይነት ፕሮጀክቶች የዜጎቿን ሕይወት ለመለወጥ አንቀሳቃሽ ሞተር ይሆናሉ”ም ብለዋል።
የኢነርጂው ዘርፍ ከእነዚህ አንዱና ዋነኛው መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የማስዳር ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ ጃሜል አል ራማሂ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለጸሐይ እና ነፋስ ታዳሽ ኃይል የሚሆን ሰፊ አቅም እንዳላት ጠቅሰው፣ በዓለም ላይ አበይት ከሚባሉት የታዳሽ ኃይል ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ማስዳር በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋይ ለማድረግ በመቻሉ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችን በጎበኙበት ወቅት የሁለቱ ሃገራት ተወካዮች በጋራ የ500 ሜ.ዋ የፀሀይ ኃይል ፕሮጀክት ላይ ለመሥራት መስማማታቸው የሚታወስ ነው፡፡