አቶ ሙስጠፌ፤ “ሁልሁል ኦፕሬሽን” አልሸባብን የደመሰሰውን የክልሉን ልዩ ሃይል ለአዲስ ተልዕኮ ወደ ድንበር ሸኙ
የሱማሌ ክልል፤ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የገባ የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን መደምሰሱን ገልጿል
በኢትዮጵያ ለሶስት ቀን በተካሄደ ዘመቻ ከ100 በላይ የአልሸባብ አባላት መገደላቸው ተገለጸ
ከአራት ቀናት በፊት "አቶ" በሚባል ቦታ ወደ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን የገባ የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን መደምሰሱን የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት በትናትናው እለት አስታውቋል።
ቡድኑ በሱማሌ ክልል "ሁልሁል" በሚባል ንዑስ ቀበሌ ከተከበበ በኋላ ሙሉ ለሙሉ መደምሰሱን ም/ቤት ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።
አልሸባብ በኤልከሬ ወረዳ አልፎ ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት መንግስት "ሸኔ" ራሱን ደግሞ "የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት" ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ለመገናኘት አልሞ እንደነበር ተገልጿል።
ቡድኑ አስቦት ወደነበረው ቦታ ሳይደርስ የያዛቸው 13 ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው የተገለጸ ሲሆን ይዞት የገባው ትጥቅና ስንቅም ተማርኳል ተብሏል። ለሶስት ቀን በተካሄደው ኦፕሬሽንም ከ100 በላይ የአልሸባብ አባላት ተገድለዋል ብሏል ክልሉ።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በዛሬው እለት በሁልሁል ቀበሌ ሰርጎ የገባውን የአልሸባብ ቡድን ለመደምሰስ የተመለሰውን የክልሉ ልዩ ሃይል ለሌላ ተልእኮ ወደ ድንበር ሸኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በአፍዴር ዞን ቆህሌ ወረዳ በሁልሁል ንዑስ ቀበሌ ላይ ሰርጎ በገባው አሸባሪው የአልሸባብ ቡድን ላይ በተደረገው ዘመቻ የተመለሰውን የክልሉ ልዩ ሃይል ነው ወደ ድንበር አሸኛኘት ያደረጉለት።
በሽኝት መርሐ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌን ጨምሮ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሙበሽር ድባድ ራጌ፣ የክልሉ ልዩ ሃይል አመራሮችና ሌሎች የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።