የሶማሊያ ጦር በመካከለኛው ሸበሌ ክልል 9 የአልሸባብ ታጣቂዎችን መግደሉን አስታወቀ
የሶማሊያ ጦር በመካከለኛው ሸበሌ ክልል 9 የአልሸባብ ታጣቂዎችን መግደሉን አስታወቀ
አልሸባብ ከሶማሊያ ጦር ጋር በተደረገው ውግያ የባላድ ከተማን ተቆጣጥርያለሁ ብሏል
የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በስተሰሜን ምስራቅ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በመካከለኛው ሸበሌ ክልል በምትገኘው የባላድ ከተማ ውስጥ ባደረገው ውጊያ፤ ዘጠኝ የአልሸባብ ታጣቂዎችን ገድሎ በርካቶችን ማቁሰሉን ባለስልጣናት ገልጿል።
የባላድ ወረዳ ኮሚሽነር ካዲም አሊ ኑር ለሶማሊያ ብሄራዊ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፤ ታጣቂዎቹ ከተማዋን ለመቆጣጠር በማሰብ ከሶስት አቅጣጫዎች ጥቃት ቢሰነዝሩም ጦር ሰራዊቱ ጥቃቱን ማክሸፍ ችሏል።
“ታጣቂዎች ከተማዋን ለመቆጣጠር ሙከራ ካደረጉ በኋላ በተካሄደው ውጊያ የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ዘጠኝ የአልሸባብ ታጣቂዎችን ገድሏል፤ ሁኔታው አሁን የተረጋጋ ሲሆን የሶማሊያ ጦር ሃይሎች የሚያካሂዱት ወታደራዊ ዘመቻ እንደቀጠለ ነው”ም ብሏል ካዲም ኑር።
በአንጻሩ የአልሸባብ ታጣቂዎች ከተማዋን መያዛቸው፣ቢያንስ አንድ ወታደር መግደለቻው እና ሌሎች ሶስት ማቁሰላቸው ተናግሯል ሲል ሲጂቲኤን ዘግቧል።
ከአይ.ኤስ.አይ.ኤስ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት አሻባሪው አልሻባባ አሁንም ድረስ የሶማሊያ ሰላም ዋነኛ ስጋት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አምስት ሀገራት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ፤የቀጠናው ስጋት የሆነው አሸባሪውን የአልሻባብ ለማዳከም በርካታ ወታደራዊ ዘመቻዎች ሲያደርጉ እና የሰላም ማስከበር ስምሪቶች ስያከናውኑ መቆየታቸውንም እንዲሁ የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ላይ በሶማሊያ ፕሬዝዳንት ፋርማጆ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ መከካል የተፈጠረው አለማግባባት ለሶስት አስርት አመታት ሰላም ርቋት የቆየችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገረ ሶማሊያ ወደ ለየለት ትርምስ እንዳያስገባት በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡