በኢትዮጵያ 14 የአልሸባብ እና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
የተያዙት የሽብር ቡድኖቹ አባላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጥቃት ለመፈጸም ተዘጋጅተው እንደነበር የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል
አባላትን በመመልመልና የሽብር ቡድኖችን አስተምህሮ በመስጠት ወደ ሶማሊያ በመላክ ስልጠና እንዲያገኙም ታቅዶ እንደነበር ተጠቁሟል
በኢትዮጵያ 14 የአልሸባብ እና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት የነበራቸው 14 የአልሸባብ እና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።
አልሸባብ እና አይ ኤስ አባሎቻቸውን ወደ አዲስ አበባ እና የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመላክ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት በመፈፀም በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳይ ለማድረስ እንዲሁም የሀገሪቱን በጎ ገፅታ ለማበላሸት በዝግጅት ላይ እንዳሉ ብሄራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን 14 የሽብር ቡድኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ አባላትን በመመለመል፣ የሽብር እቅድ በማውጣትና ኢላማዎችን በመለየት እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጥቃቶችን ለመፈጸም ስምሪት ወስደው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበሩ ተጠርጣሪ የሽብር ቡድኖቹ አባላት እንዲያዙ ተደርጓል።
ይሄንን የጥፋት ተግባር ለመፈፀም ሀገር ውስጥ የገባው አንደኛው የአልሸባብ የሽብር ቡድን አብዱል አብዲ ጀማል በቅፅል ስሙ አብዱልቃድር የተባለ ተጠርጣሪ አንዱ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የአልሸባብን የሽብር ህዋስ ሲያስተባብር የነበረና፤ በሶማሊያ ከሚገኘው ጃፋር ወይም ጉሬ ከተባለ የአልሸባብ ከፍተኛ አመራር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠርና ስምሪት በመቀበል በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ወደ አዲስ አበባ ገብቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
መረጃውን ቀድሞ ያገኘውና ክትትል ሲያደርግ የቆየው ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የግንኙነት መረቡን ሲያጠና ቆይቶ አብዱል አብዲ ጀማልን ጨምሮ አብዱራህማን አደን አቡበከር፣ ሙክታር ጋብ ጎሳ፣ ጋማዕ ድርዬ አብዲ፣ ሼህ አህመድ ኑር መሀመድ ኡስማን፤ ኩሶው አደን ሁሴን፤ መሀመድ ሀሰን አደንና ኡመር ሬዲዋን ሙሃዲ ከተባሉ የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።
በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት እንደሚፈጽም ሲዝት የነበረው የአይኤስ የሽብር ቡድንን ህዋስ በሀገር ውስጥ ሲያስተባብር የነበረው አማን አሰፋ ገዲምወርቅ የተባለው ተጠርጣሪ ባደራጃቸው የጥፋት ቡድኖች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ በብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በተደረገበት ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።
ተጠርጣሪው ለረጅም ጊዜ የአይኤስ አባል የነበረና ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የጥፋት ቡድኖችን ሲያደራጅም ነበር ተብሏል።
አይ ኤስ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን መረጃው የደረሳቸው የኢትዮጵያ የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት ባደረጉት ክትትል የቡድኑ ህዋስ አስተባባሪ የሆነውና ከሶስት በላይ የሀሰት ስሞችን የሚጠቀመው አማን አሰፋ ገዲምወርቅን ጨምሮ የሽብር ቡድኑ አባላት የሆኑት ፉአድ ሽፋ ከድር፣ አብዱልጀባር አብደላ ኢብራሂም፣ ሰይድ ሙስጠፋ ኢብራሂም፣ መሱድ ሳጂቦ ገበየሁና ተፈራ በላይ ተሾመ ወይም እድሪስ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የአልሸባብና የአይኤስ ቡድን አባላቱ የወጠኑትን የሽብር ጥቃት ለማሳካት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አባላትን በመመልመል፣ በማደራጀት፣ ስምሪት በመስጠት እንዲሁም የእነርሱን አስተምህሮዎችም ለማስረጽ ሲሰሩ መቆየታቸውን መግለጫው አመልክቷል።
የሽብር ቡድኖቹ አባላትና ግብረ አበሮቻቸው ጥቃት ለመፈጸም ዒላማ ያደረጓቸውን ስፍራዎች ቅኝት አድርገውና መርጠው፤ የሚጠቀሙባቸውን መሳሪያዎችም አዘጋጅተው እንደነበር የጠቆመው መግለጫው፤ የሽብር እቅዱ በደህንነት መስሪያ ቤቱ ክትትል ይደረግበት ስለነበር ምንም አይነት ጥቃት ሳይፈፀም ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ ይገኛል ብሏል።
የአልሸባብም ሆነ የአይኤስ ቡድኖች በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ የሽብር ጥቃት እንዲፈጽሙ ዕቅዶችን የሚያወጡት፣ ስምሪት፣ አመራርና ድጋፍ የሚሰጡት በተለያዩ አገራት የሚገኙ አካላት መሆናቸውን ያመለከተው መግለጫው፤ በኢትዮጵያ የተመለመሉ የቡድኑ አባላትም በሀገሪቱ ጥቃት ለመፈጸም እንዲያስችላቸው ወደ ሶማሊያ ተልከው ስልጠና እንዲያገኙ እቅድ እንደነበርም ተጠቁሟል።
የአልሸባብና የአይኤስ የሽብር ቡድኖች ለመፈጸም ያቀዱትን ጥቃት ለማክሸፍ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ረዘም ላለ ጊዜ ጥናታዊ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱንም መግለጫው አያይዞ አመልክቷል።
የሽብር ቡድኑ አባላት አሁን ላይ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ጥቅት ለመፈፀም እንቅስቃሴ ለማድረግ የሞከሩት፤ “በጁንታው” ጥቂት የሕወሓት የጥፋት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም በማሰብ እንደነበር በመግለጫው ተመላክቷል።
ኢቢሲ እንደዘገበው እነዚህ አሸባሪዎች የጥፋት ተልዕኳቸውን ለማስፈፀም የሚጠቀሙባቸው የግንኙነት መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሳቁሶችም በቁጥጥር ስር እንዲውሉም ተደርጓል።
የሽብር ቡድኑን አባላት በመከታተል በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ለማድረግ በተካሄደው ሰፊ የኦፕሬሽን ስራም ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፤ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ የአማራ፤ የኦሮሚያና የሱማሌ ክልል የፀጥታ አካላት በቅንጅት መስራታቸውን ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በመግለጫው አስታውቋል።
በቀጣይም የሽበር ቡድኑ በኢትዮጵያ ጥቃት ለመፈፀም ካለው ዝግጅት አንጻር ህዝቡ ይሄን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደረግና የተለየ ነገር ሲመለከትም በአካባቢው ላለ የፀጥታ አካል መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል።