ኦብነግ “መንግስት የሶማሌ ክልልን ስምና ባንዲራ ለመቀየር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የሚወጡ መረጃዎች ያሳስበኛል አለ
ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ በክልሉ ወታደራዊ ኃይል መጠናከር ወታደራዊ አስተዳደርን ሊያስከትል ይችላል በሚል ሶማሌ ክልልን አስግቷል ብሏል
መንግስት ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ እና ባነሳቸው ሀሳቦች ዙርያ እስካሁን ምንም አላለም
መንግስት “የሶማሌ ክልልን ስም እና ባንዲራ ለመቀየር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ” የሚወጡ መረጃዎች እንዳሳሰቡት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) አስታወቀ።
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሌ ክልል እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ህገ መንግስታዊ መብቶችን እና በኦብነግ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት የሚጥስ ነው ሲል ወቀሰ፡፡
ድርጅቱ በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ “መንግስት የሶማሌ ክልልን ሥምና ባንዲራ ለመቀየር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ እየወጡ ያሉ ጭምጭምታዎች አሳስበውኛል” ነው ያለው፡፡
በተጨማሪም “የትኛውንም የሶማሌ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል እና ገጽታ እንደሚሻር የሚገልጹ መረጃዎች መውጣታቸው ተገቢነት የሌለው እና የክልሉንም ዜጎች ማንነት የሚፍቅ ነው” ብሎታል፡፡
ባለፉት ሶስት አስርተ ዓመታት የክልሉ ነዋሪ እንደ ዜጋ ተጨቁኖ፣ የሰበአዊ መብት ጥሰት እና የግጭት ሰለባ ሆኑ የቆየባቸው ጊዜያት ዳግም ሊመለሱ አይገባም ሲል አመላክቷል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም “የሶማሌ ሽማግሌዎች፣ ሴቶች እና ሌሎች የማህበረሰብ አባላት በቴሌቭዥን ቀርበው የሶማሌ ማንነታቸውን በመካድ ራሳቸውን እንዲያዋርዱ ተደርገዋል” ነው ያለው፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ የሚገኙት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ ባለበት ወቅት መሆኑም ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ስለመሆኑ ገልጿል፡፡
ፓርቲው ተፈጥረዋል ያለቸውን ድርጊቶች በጽኑ እንደሚያወግዝ አንስቶ የፌደራል መንግስቱ አፋጣኝ ማስተካከያዎችን እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል በተፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት የተነሳ የሶማሌ ሕዝብ ሰለባ እንዳይሆን መንግሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልገውም አሳስቧል፡፡
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) በክልሉ ወታደራዊ ኃይል እና እንቅስቃሴ መጠናከር ወታደራዊ አስተዳደርን ሊያስከትል ይችላል በሚል ሶማሌ ክልልን አስግቷል ሲል በመግለጫው አካቷል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት የሶማሌን ሕዝብ ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች እና የሰላም ስምምነቱን እንዲያከብር ይህ ካልሆነ የክልሉን ሰላም አደጋ ውስጥ የሚከት ጉዳይ ሊፈጠር እንደሚችል እንደሚያባብሰው ገልጿል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው በኢትዮጵያን ሕገ መንግስት አንቀጽ 39 ስር የተደነገገውን ማንኛውም ብሔር ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን በመጠቀስ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሁሉም ዜጎቹ የእኩልነት መርህን ማስከበር አለበት ሲል አክሏል፡፡
በፈረንጆቹ 2018 ከፌደራል መንግስት ጋር በተደረሰው የሰላም ስምምነት በትጥቅ ትግል ላይ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) በሰላማዊ ፖለቲካ ለመታገል ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ይታወሳል፡፡
ኦብነግ በመግለጫው ላቀረባቸው ወቀሳ እና ክሶች ከመንግስት በኩል እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡