ቱርክ ግንኙነታቸው የሻከረውን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ማደራደር መጀመሯ ተነገረ
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአንካራ ተጀምሯል ስለተባለው ድርድር ምንም መናገር እንደማይፈልግ ለአል አይን አማርኛ ገልጿል
የሶማሊያ መንግስትም በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ማብራሪያ አልሰጠም
ቱርክ ግንኙነታቸው የሻከረውን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ማደራደር መጀመሯ ተነገረ።
ሬውተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው ድርድሩ በአንካራ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
ይሁን እንጂ አደራዳሪዋ ቱርክም ሆነች ተደራዳሪዎቹ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም።
የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሙአሊም ፊቂ የመሩት ልኡክ በትናንትናው እለት ወደ ቱርክ ማቅናቱን ቢዘግቡም የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማረጋገጫ አልሰጠም።
አል ዐይን አማርኛ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣንም በአንካራ ተጀምሯል ስለተባለው ድርድር ምንም መናገር አንፈልግም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የሶማሊላንድ መንግስት ቃል አቀባይ በበኩላቸው በድርድሩ ላይ እየተሳተፉ እንዳልሆነ ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጥር ወር ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በደረሰችው የወደብ ስምምነት ምክንያት የአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ ግንኙነት መሻከሩ ይታወቃል።
ሶማሊላንድ የግዛቴ አካል ናት የምትለው ሶማሊያ በጥር ወር የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት “ህገወጥ እና ሉአላዊነቴን የተዳፈረ ነው” በሚል የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዳለች።
በሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላዎች እንዲዘጉ ወስና የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሀገሪቱ እንዲወጡ ማድረጓ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ካልሰረዘች በሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎችን አስወጣለሁ ማለቷም አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለወራት የዘለቀውን ውጥረታቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥረት መጀመሯ የተነገረላት ቱርክ የሶማሊያ መንግስት አጋር ናት።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በፈረንጆቹ 2011 በሞቃዲሾ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ አንካራ የሶማሊያ የጸጥታ ሃይሎችን ማሰልጠን የጀመረች ሲሆን፥ ትምህርትቤቶች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችንም ስትገነባ ቆይታለች።
ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ስምምነት ከደረሱ ከአንድ ወር በኋላም ቱርክና ሶማሊያ የ10 አመት የወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።
ስምምነቱ ቱርክ የሶማሊያን የባህር ሃይል ለማጠናከርና የሽብር ስጋትን በጋራ ለመመከት የሚያስችል ነው ተብሎ ነበር።
የሶማሊያን የባህር ክልል ለመጠበቅ ትውላለች የተባለች የቱርክ መርከብም በቅርቡ ሶማሊያ መድረሷ ይታወሳል።
ከኢትዮጵያም ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ቱርክ፥ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የገቡበትን ሰጣገባ በድርድር ለማስታረቅ ሸምጋይ ሆናለች ተብሏል።