አረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትና የትብብርን የሚያጎለብት ነው አለች
አረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያና ሶማሊያን የአንካራ ስምምነት ታሪካዊ በማለት አወድሳዋለች

ኢምሬትስ ቱርክና የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን ስምምነቱ እንዲደረስ ያደረጉትን ጥረት አድንቃለች
አረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያና ሶማሊያ ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትና የትብብርን የሚያጎለብት ነው በማለት አደነቀች።
በቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አደራዳሪነት በአንካራ ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ድርድር በስምምነት ተቋጭቷል።
ይህንን ተከትሎም የአረብ ኢምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን ታሪካዊ ስምምነት በደስታ እንደምትቀበል አስታውቋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አለመግባባታቸውን እንዲፈቱ የውይይት ድልድዮችን ያጠናክራል ያለው ሚኒስቴሩ፤ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያለውን መረጋጋት እና የትብብር መንፈስ እንደሚያጠናክር እምነቱን ገልጿል።
የአረብ ኢምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው፤ ቱርክና የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን ኢትዮጵያና ሶማያ ከስምምነት አንዲደርሱ ያደረጉትን ጥረትም አድንቋል።
አረብ ኤምሬትስ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ከሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ጋር የጠበቀ እና ልዩ የሆነ ግንኙነት እንዳላት ሚኒስቴሩ አረጋግጧል።
ሚኒስቴሩ አክሎም አረብ ኤሚሬትስ ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር እንዲሁም ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አስፈላጊነት ላይ ያላት ቁርጠኝነት አረጋግጧል።
ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር በአዲስ አበባ የወደብ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባውን ስምምነት ተከትሎ ሶማሊያ ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በሚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አቋርጣም ነበር፡፡
የሁለቱም ሀገራት ወዳጅ የሆነችው ቱርክ በአንካራ የውይይት መድረክ ያዘጋጀች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድ በትናንትናው ዕለት ወደ አንካራ አቅንተው ተወያይተዋል፡፡
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የሁለቱን ሀገራት መሪዎች በተናጠል አግኝተው እንዳወያዩ እና ልዩነቶቻቸውን በስምምነት ለመፍታት መስማማታቸውም ታውቋል።
የአንካራ ስምምነት የሚል ስም የተሰጠው ይህ ሰነድ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ለማክበር የተስማማች ሲሆን የባህር በር ፍላጎቷንም ይህን በማይጥስ መልኩ ታካሂዳለች ብሏል፡፡