ብሔራዊ ባንክ ከምንዛሬ ስርአት ለውጥ በኋላ ወርቅ የሚገዛው በአለምአቀፍ እለታዊ ዋጋ መሆኑን ገለጸ
ባንኩ እንደገለጸው ለወርቅ አቅራቢዎች ክፍያ የሚፈጽመው የእለቱ አለምአቀፍ የወርቅ ዋጋ ብሔራዊ ባንክ በእለቱ ለወርቅ ግዥ በሚያወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን ተባዝቶ ነው
ብሔራዊ ባንክ ከትናንት ጀምሮ በገበያ ወይም በአቅርቦት እና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ስርአት ተግባራ አድርጓል
ብሔራዊ ባንክ ከምንዛሬ ስርአት ለውጥ በኋላ ወርቅ የሚገዛው በአለምአቀፍ እለታዊ ዋጋ መሆኑን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ስርአቱ በገበያ እንዲወሰን ካደረገበት ከሐምሌ 22፣2016 ዓ.ም ጀምሮ ወርቅ የሚገዛው በእለቱ የአለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ ነው ብሏል።
ባንኩ እንደገለጸው ለወርቅ አቅራቢዎች ክፍያ የሚፈጽመው የእለቱ አለምአቀፍ የወርቅ ዋጋ ብሔራዊ ባንክ በእለቱ ለወርቅ ግዥ በሚያወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን ተባዝቶ ነው።
በእየለቱ በምን ያህል የውጭ ምንዛሬ ወርቅ እንደሚገዛ በጽረ-ገጹ ይፋ እንደሚያደርግ የገለጸው ባንኩ፣ የወርቅ አምራቾች እና ሻጮች ወርቁን በሸጡበት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ክፍያ ይፈጸምላቸዋል ብሏል። ወርቅን በብቸኝነት የሚገዛው ብሔራዊ ባንክ ነው።
ብሔራዊ ባንክ ከትናንት ጀምሮ በገበያ ወይም በአቅርቦት እና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ስርአት ተግባራ በማድረግ ትልቅ የሚባል የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ አድርጓል።
ባንኩ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ያሰገኛል ያላቸውን ጥቅሞች በመዘርዘር የውሳኔውን አስፈላጊት ዘርዝሯል።
ባንኩ የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኝ ስራ የተሰማሩ ሰዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ የውጭ ምንዛሬው በተገቢው መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ፣ በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱሰትሪዎች እንዲበረታቱ እና የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ኢንዲገቡ ማበረታታት እና ህጋዊ ያልሆኑ የውጭ ምንዛሬን ግብይትን ማስቀረት የገበያ መር ምንዛሬ ስርአቱ ዋና ዋና ጠሜታዎች ናቸው ብሏል፡፡
ነገርገን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በገቢ ንግድ ላይ የተመሰረተ ወይም የንግድ ሚዛኑ ወደ ኢምፖርት (ገቢ) ንግድ ማዘንበሉ እና የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ገበያ መር የሆነውን የውጭ ምንዛሬ ስርአት መሸከም የሚችል አለመሆኑን ባለመያዎች እየተናገሩ ናቸው።
ባንኩ ይህን የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉ መንግስት ብድር እንዲያገኝ አስችሎቻል።
መንግስት ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ጋር ብድር ለማግኘት ረዘም ላለ ጊዜ ድርድር ሲያደርግ ቆይቷል።
አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ብድር ለመስጠት፣ የኢትዮጵያ መንግሰት የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያደርግ ሲጠይቅ እንደነበር እና ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛው በገበያ የሚወሰን የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል።
መንግስት ይህን የውጭ ምንዛሬ ስርአት ይፋ ባደረገበት በትናንትናው አይኤምኤፍ የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ማድረጉን አስታውቋል።