ኢትዮጵያ ድርሻ ባላት በርበራ ወደብ መርከብ ማሰማራት ጀመረች
በርበራ የገባችው ጊቤ መርከብ 11 ሺህ 200 ቶን ዕቃ ይዛ ለሶማሌላንድ ገበያ አቅርባለች
ሸበሌ የተሰኘች መርከብም ከሳምንት በኋላ ወደቡ ላይ ትደርሳለች
ኢትዮጵያ 19 በመቶ ድርሻ ባላት የበርበራ ወደብ መርከብ ማሰማራቷን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ የመጀመሪያ የሆነችው ጊቤ መርከብም በርበራ ወደብ መግባቷ ተገልጿል።
“ድርጅታችን ወደ በርበራ ወደብ መደበኛ አገልግሎት መስጠት የጀመርንበት የመጀመሪያውን ታሪካዊ ጉዞ ጊቤ በተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ ማሳካት የቻልን መሆኑን በደስታ እንገልፃለን” ሲል ድርጅቱ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።
በግቤ መርከብ የተጀመረው አገልግሎት እንደሚቀጥልና ሸበሌ የተባለችው መርከከብም ከሳምንት በኋላ በርበራ ወደብ እንደምትደርስም ይጠበቃል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ግቤ መርከብ ወደ በርበራ ወደብ ስትገባ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ፣ በሱማሌ ላንድ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል ሰኢድ ሙሃመድ ጅብሪል እንዲሁም የዱባይ ፖርት (DP World) ተወካዮች ተገኝተው የስራ ሂደቱን ጎብኝተዋል ተብሏል።
ጊቤ እና ሸበሌ መርከቦች በ “ገልፍ ኢንዲያ ሰብ ኮንትነት” ውስጥ ባለው መስመር እቃን የማጓጓዝ ስምሪት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ሲሆን ወደ በርበራ ወደብ የተጀመረው አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ የድርጅቱን አገልግሎት ሽፋን ለማስፋትና ለማሳደግ የተያዘ ዕቅድ አንድ አካል መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም የበርበራ ኢትዮጵያ ኮሪደር ለሀገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ ተወዳዳሪ አገልግሎት የሚሰጥበትን ቀጣይ ሥራ መሠረት ከማስቀመጥ አንፃር ከፍትኛ ይኖረዋል ተብሎም ይጠበቃል።
እንደ ድርጅቱ መግለጫ፤ ጊቤ መርከብ በአሁኑ ጉዞዋ 11 ሺህ 200 ቶን የፍጆታ ዕቃ ይዛ ለሶማሌላንድ ገበያ አጓጉዛለች፤ ሸበሌ መርከብም ተመሳሳይ መጠን ያለው ዕቃ ትጭናለች ተብሏል።
በወደቡ ላይ የተሰማሩ በርካታ ባለ ሃብቶችና ሀገራት ከፍተኛ የማልማትና የመገልገል ጥያቄ ማቅረባቸውና የስራ ፍላጎት ማሳየታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የበርበራ ወደብም ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትና አመቺነት ጨምሯል ተብሏል።
በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት ታሪክ የኢትዮጵያ መርከቦች ወድ በርበራ ወደብ ጉዞ ሲያደርጉ ከ 20 ዓመት በኋላ የጊቤ መርከብ የመጀመሪያዋ መሆኗን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ዕቃዎቿን ከምታጓጉዝበት ጅቡቲ ወደብ ባለፈ አማራጭ ወደቦችን በማማተር ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡
የበርበራ ወደብን፤ ዲ ፒ ወርልድ 51 በመቶ፣ ሶማሌላንድ 30 በመቶ እና ቀሪውን 19 በመቶ ድርሻ ኢትዮጵያ እንደሚይዙት መገለጹ ይታወሳል።
የወደቡ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ የኮንቴይነር ተርሚናል የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ እና የዲፒ ወርልድ ዳይሬክተር ሱልጣን ቢን ሱለይማን በተገኙበት ከሳምንት በፊት በይፋ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።