ምርመራው ከአሁን ቀደም በኮቪድ-19 ተይዘን እና ሰውነታችን መድህኖችን (immunities) አዘጋጅቶ እንደሆነ የሚታወቅበት እንጂ በቫይረሱ መያዛችን በቀጥታ የሚረጋገጥበት አይደለም
ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 20 ቀናት ውስጥ አደርገዋለሁ ያለችው የ‘አንቲቦዲ’ ምርመራ ምንድነው?
ኢትዮጵያ ከዛሬ ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ሀምሌ 7 ድረስ የኮቪድ-19 አንቲቦዲ (Antibody) ምርመራን ልታካሂድ ስለመሆኗ አስታውቃለች፡፡
ምርመራው እስከ ሀምሌ 7 ቀን 2012 ዓ/ም ድረስ አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች ይካሄዳል ያለው የጤና ሚኒስቴር በሽታው በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ስርጭት ለማወቅ እና ምላሽ ለመስጠት እንደሚረዳ ገልጿል፡፡
የአንቲቦዲ ምርመራ ኮቪድ-19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው የቅኝት ዳሰሳ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢኖረውም ከምርመራው የሚገኘውን ውጤት ብቻ ተጠቅሞ ህክምና መስጠት አይቻልም፡፡
ሚኒስቴሩ ቫይረሱን በላቦራቶሪ መመርመር ከጀመረበት ከጥር 29 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ቫይረሱ ያለበትን ሰው ለመለየት የሚያስችል 216 ሺ 328 ሞለኪዩላር ምርመራ ማድረጉንም አያይዞ ገልጿል፡፡
ህብረተሰቡ፣ የጤና ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለትግበራው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቋል፡፡
ለመሆኑ የአንቲቦዲ ምርመራ ምንድነው ለምንስ ያገለግላል አል ዐይን አማርኛ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያገኛቸውን መረጃዎች በሚከተለው መልኩ አጠናቅሯቸዋል፡፡
አንቲቦዲ ወይም ጸረ እንግዳ አካል ምንድነው?
አንቲቦዲ ወይም ጸረ እንግዳ አካል በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ የፕሮቲን ቅንጣቶች ናቸው፡፡ ሰውነታችን ራሱን ከበሽታዎች እንዲጠብቅ እና ቀደም ሲል ይዞን በነበረው በሽታ ዳግም እንዳንጠቃ የሚከላከሉልን ወይም የሚያድኑን ናቸው፡፡
ሰውነታችን ሊያዘጋጅ የሚችለው መድህን (immunity) ግን እንደየበሽታዎቹ ዓይነት ይለያያል፡፡ ሰውነታችን በኩፍኝ ከተጠቃን በኋላ ሊያዘጋጅ የሚችለው ጸረ እንግዳ አካል ከሌላ በሽታ ሊያድነን ግን አይችልም፡፡
እንዴት ይካሄዳል?
ሚኒስቴሩ አደርጋለሁ ያለው የአንቲቦዲ ምርመራም በዋናነት የደም ናሙናዎችን በመውሰድ የሚካሄድ ነው፡፡ ከ3-5 ሚሊ ሊትር ደም ናሙናዎችን በመውሰድ ይካሄዳልም፡፡ በደም ውስጥ ያሉት አንቲቦዲዎች ናቸው ከአሁን ቀደም ኮቪድ-19ን በሚያስከትለው ቫይረስ ተይዘን እንደሆነ ለማወቅ በሚያስችል መልኩ የሚመረመሩት፡፡
ምርመራው ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው የቅኝት ዳሰሳ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ሆኖም ከምርመራው የሚገኘውን ውጤት ብቻ ተጠቅሞ ህክምና ለመስጠት አይቻልም፡፡ ቀጥታ በቫይረሱ መያዛችንንም ሳይሆን ከአሁን ቀደም ተይዘን እና ሰውነታችንን መድህኖችን (immunities) አዘጋጅቶ እንደሆነ ለማወቅ ብቻ የሚደረግ የምርመራ ዓይነት ነው፡፡
አንድ ሰው በቫይረሱ መያዝ አለመያዙን ለማረጋገጥ የቫይረስ ምርመራ (Viral Test) ነው የሚደረገው፡፡ ምርመራው አፍና አፍንንጫችንን ከመሳሰሉ የስርዓተ ትንፈሳ አካላት ናሙናዎችን በመውሰድም ይካሄዳል፡፡ የምርመራው ውጤትም በአንድ እስከ ሁለት ቀናት ውስጥ ይታወቃል፡፡ የአንቲቦዲ ምርመራ ግን ዘለግ ያለ ጊዜን ሊወስድ ይችላል፡፡
የአንቲቦዲ የምርመራ ውጤቶች ምንን ያሳያሉ?
አንቲቦዲን በመመርመር የሚገኙ ውጤቶች ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሁሉ ከአሁን ቀደም ኮቪድ-19ን በሚያስከትለው ቫይረስ ተይዘን እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችሉ ናቸው፡፡
ውጤቱ ፖዘቲቭ የሚሆን ከሆነ ከአሁን ቀደም ኮቪድ-19ን በሚያስከትለው ቫይረስ አለበለዚያም ጉንፋን ኢንፍሉዌንዛን በመሳሰሉ ተመሳሳይ የቫይረስ ዝርያዎች ተይዘን ነበር ማለት ነው ከአሜሪካ የበሽታዎች መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል የተገኙት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፡፡
ሆኖም ከአሁን ቀደም ኮቪድ-19ን በሚያስከትለው ቫይረስ ተይዘን ሰውነታችን ያዳበራቸው አንቲቦዲዎች አሁንም ቫይረሱ ለመከላከል ያስችሉን አያስችሉን እንደሁ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ እስከመቼ ለመከላከል ያስችላሉ ስለሚለውም ገና አልታወቀም፡፡
የምርመራ ውጤታችን ኔጌቲቭ የሚሆን ከሆነ ከአሁን ቀደም ኮቪድ-19ን በሚያስከትለው ቫይረስ አልተያዝንም ነበር ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ይህ አሁንም ላለመያዛችን ዋስትና አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሰውነታችን አንቲቦዲውን ለማዘጋጀት እስከ ሶስት ሳምንታት ሊወስድበት ይችላልና፡፡ ምናልባትም አንቲቦዲው በሚዘጋጅባቸው በነዚሁ ሳምንታት የምንጋለጥበት አጋጣሚ ካለ በቫይረሱ ልንያዝ ወደ ሌሎች ልናስተላልፍም እንችላለን ማለት ነው፡፡