ኢትዮጵያ ለተመድ በጻፈችው ደብዳቤ “ግብጽ እና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ድርድር እንዲያከብሩ”ጠየቀች
ግብጽ እና ሱዳን “የድርድሩን ሂደት በማኮላሸትና አለምአቀፋዊ በማድረግ ጫና ማሳደርን መርጠዋል”ም ነው ኢትዮጵያ በደብዳቤው ያለችው
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ስለሚመራው የሶስትዮሽ ድርድር ያላትን አቋም ለተመድ የጸጥታው ም/ቤት በደብዳቤው አሳውቃለች
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት በሚመራው “የሶስትዮሽ ድርድር ላይ ያላትን የፀና አቋም” ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ አስታወቀች ፡፡
“ግብፅ እና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌትና አስተዳደርን በማስመልክት ወደሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲመለሱ፤ እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የድርድር ሂደት እንዲያከብሩ ሊያስስቧቸው ይገባል” ስትል ጥሪ አቅርባለች ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለወቅቱ የም/ቤቱ ፕሬዝዳንት በላኩት ደብዳቤ “በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ሂደት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም / ቤት የተሟላ ድጋፍ ያለው፣ መርሆዎችን መሠረት ያደረገና በአፍሪካ ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን በማፈላለግ መንፈስ የተቃኘ” መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ጥልቅ ፍላጎት ቢኖርም ፤ግብፅ እና ሱዳን ሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚ ወደሚያደርገው መፍትሄ ለመምጣት በሚያስችል ቅን ልቦና እየተደራደሩ እንዳይደለም ነው አቶ ደመቀ በደብዳቤው የጠቀሱት፡፡
ሃገራቱ ድርድሩን “በማኮላሸት” እና ጉዳዩን “ዓለም አቀፍ በማድረግ” በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደርን መምረጣቸውንም ነው የገለፁት፡፡
ደብዳቤው ኢትዮጵያ በህብረቱ በሚመራው የሶስትዮሽ ድርድር የማይናወጥ ቁርጠኝነት እና እምነት እንዳላት ያስረግጣል፡፡
ደቡብ አፍሪካ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጉዳዩን ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ ለመፍታት ላደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ያላትን አድናቆትም ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በመጪው ክረምት ከመፈጸሙ በፊት መረጃ ለመለዋወጥ ያደረገችውን ጥረትም አስታውሷል ምንም እንኳን ጠይረቷን ሁለቱም የታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት ባይቀበሉትም፡፡
ሃገራቱ በአስገዳጅ ስምምነት ስም ኢ-ፍትሐዊ ሁኔታዎችን ለማስጠበቅ እና በግድቡ ውሃ እንዳትጠቀም ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት እንደሌለውም ኢትዮጵያ በደብዳቤው አስታውቃለች፡፡
የሶስቱ ሃገራት መሪዎች እ.ኤ.አ በ2015 በሱዳን ካርቱም ለፈረሙት የመርሆዎች ስምምነት ያላትን ቁርጠኝነትም ገልጻለች ግብጽ እና ሱዳን በስምምነቱ የገቡትን ቃል አለመጠበቃቸውን በመጠቆም፡፡
ከዚህ ውጭ ጫና ለማድረግ የሚደረጉ የትኛውም ዓይነት ሙከራዎች እና ድርድሩን ከህብረቱ ውጭ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች በሃገራቱ መካከል ያለውን መተማመን የበለጠ እንደሚጎዱ ነው ኢትዮጵያ በደብዳቤው የገለጸችው፡፡