ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት በይፋ ጥያቄ አቀረበች
ጠቅላይ ሚኒስትር ጠ/ሚ ዐቢይ “ኢትዮጵያ በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት አቅም አላት” ብለዋል
ካፍ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያቀረበችውን ጥያቄ ኮሚቴው እንደሚመክርበት አስታውቋል
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት በይፋ ጥያቄ አቅርባለች።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 46ኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት ምሽት በጉባዔው ላይ ለመካፍ አዲስ አበባ ለገቡት የፊፋ እና የካፍ አመራሮች በታላቁ ቤተ-መንግስት የእራት ግብዣ አዘጋጅተዋል።
በዚሁ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ በይፋ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግርም “ኢትዮጵያ በ2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት አቅም አላት” ብለዋል።
የካፍ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ያላትን ታሪካዊ ድርሻ ከግምት በማስገባት በፈረንጆቹ በ2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫውን ተጠቅማ የአፍሪካን እግር ኳስ ለማሳደግና በስፖርቱ አገር ለመገንባት እንደምትሰራ መናገራቸውንም ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አክለውም፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ስታዲየሞች እየገነባች መሆኑን እና ያሉት ላይም ማሻሻያ እያደረገች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ካፍ የኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ ተቀብሎ እንዲያጸድቅም ፕሬዝዳንት ታዬ ጠይቀዋል።
የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሙትሴፔ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያቀረበችውን ጥያቄ ካፍ ከኮሚቴው ጋር እንደሚመክርበት ገልዋጸል።
የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄዋን ያቀረበችው በትክክለኛው ጊዜ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ለእግር ኳስ ያላቸው ስሜት እና ቁርኝት ከፍተኛ መሆኑን እረዳለሁ ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሕዝቡን አንድ የሚያደርግ ትልቅ አቅም መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞችና የስፖርት መሰረተ ልማቶችን እንዳስጎበኟቸውና ባዩት ነገር መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ ካፍ ባሉት የአሰራር ስርዓቶች እንደሚታይ አመልክተዋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 46ኛ ጠቅላላ ጉባዔ በዛሬው እለት የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሙትሴፔ በተገኙበት በስካይ ላይት ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።