ኢትዮጵያ በ2 ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የቀየረችው “ዓባይ ፪” መርከብ ጅቡቲ ደርሳለች
2 ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በግዙፍ የእቃ ጫን መርከብ በድርድር መቀየራቸው ይታወሳል
በቅያሪ የተገኘችው መርከብ “ዓባይ ፪” የሚል መጠሪያ የተሰጣት ሲሆን፤ 63,229 ቶን የመጫን አቅም አላት
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በ2 ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ምትክ በድርድር የተቀየረችው “ዓባይ ፪” መርከብ ጅቡቲ ደርሳለች።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በቅርቡ ሊኪሳራ ዳርገውኛል ያላቸውን 42 ሺህ ሜትሪክ ቶን የመጫን አቅም ያላቸው ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መድርድር መቀየሩን ማሳወቁ ይታወሳል።
ድርጅቱ በሁለት መርከቦች ምትክ የቀየራት “ዓባይ ፪” በትናትናው እለት ጅቡቲ የደረሰች ሲሆን፤ በጅቡቲ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል።
“ዓባይ ፪” መርከብ በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ ግዙፉ የእቃ ጫኝ መርከብ መሆኗ የተገለፀ ሲሆን፤ የባሕር ትራንስፖርት ስራውን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እንደሆነ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ አስታውቋል።
በቅያሪ የመጣችው “ዓባይ ፪” መርከብ 63 ሺህ 229 ቶን የመጫን አቅም ያላት መሆኑንም ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በቻይናው ያንግዡ ዳያንግ ሺፕ ቢዩልዲንግ የተገነባው ይህ “ዓባይ ፪” መርከብ 200 ሜትር ርዝመት አለው።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ድርጅት የመርከቦቹን ቅያሪ አስመልክቶ ከዚህ ቀደም በሰጠው መብራሪያ በቅያሪ የተሰጡት ባህርዳርና ሀዋሳ የተሰኙት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከ11 ዓመታት በፊት ታሳቢ ተደርጎ የተገዙት የሀገሪቱን ነዳጅ እንዲጭኑ ነበር ብሏል።
የነዳጅ ጫኝ መርከቦቻችን የመጫን አቅም 42 ሺህ ቶን ሲሆን ይህም መካከለኛ የመጫን አቅም ካላቸዉ መርከቦች መካከል የሚያስመድባቸዉ ቢሆንም በዚሁ ምድብ ከሚገኙ እና እስከ 50ሺ ቶን የመጫን አቅም ካላቸዉ መርከቦች አኳያ ሲታይ ከካታጎሪወ የታችኛዉ እርከን ላይ የሚያስቀምጣቸዉ በመሆኑ ተፈላጊነታቸዉ ቀንሶ ለሌሎች ኩባንያዎች አከራይቶ ለመጠቀም ፈተና ሆኖ ነበር ሲሊም ገልጿል።
ይህም በየጊዜው ለእለት ከ እለት መርከብ ማንቀሳቀሻ፣ ለነዳጅ እና ለመርከበኞች ይወጣ የነበረው ወጭ ድርጅቱን ለኪሳራ እየዳረገው ስለመምጣቱ በተለያዩ ግዜያትም ጭምር በጥናት ማረጋገጡንም ጠቅሷል።
በዚሀም መሰረት ባህርዳርና ሃዋሳ የተሰኙት እነዚህን ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በድርጅቱ ታሪክ በግዝፈቱ የመጀመሪያ በሆነው 63,500 ቶን የመጫን አቅም ባለዉ መርከብ በድርድር መቀየራቸውንም ነው የገለፀው።
"አባይ ፪" የተሰኘ ግዙፍ መርከብ የአፈር ማዳበሪያና መሰል ጭነቶችን የማጓጓጓዝ ስራን በራስ አቅም ለማከናወን የሚረዳ እንደሆነም ነው ድርጅቱ የገለጸው።