ኢትዮጵያ በግዛቷ የሚያልፉ ሳተላይቶችን መረጃ መቀበል የሚያስችል ቴክኖሎጂ መግጠሟን ገለጸች
ከሁለት ዓመት በፊት የመጠቀችው የኢትዮጵያ ሳተላይት የአገልግሎት ጊዜዋ አብቅቷል ተብሏል
ኢትዮጵያ ETRSS2 የተሰኘች ሶስተኛ ሳተላይት በቅርቡ እንደምታመጥቅ ተገልጿል
ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ያመጠቀቻት ሳተላይት የአገልግሎት ጊዜዋ ማብቃቱ ተገለጸ፡
ኢትዮጵያ ከሶስት ዓመት በፊት ETRSS1 የተሰኘች ሳተላይት በቻይና አጋዥነት ወደ ህዋ ማምጠቋ ይታወሳል፡፡
ይህች ሳተላይት በቻይና እንድትመጥቅ ቢደረግም እንጦጦ በሚገኘው ማዕከል በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ቁጥጥር ሲደረግባት መቆየቱን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሺያል ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የየሳተላይት ኦፕሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር መላኩ ሙካ ለዓልዐይን እንዳሉት አንድ ETRSS1 ሳተላይት ወደ ህዋ የተላከችው ለሁለት ዓመት አገልግሎት እንድትሰጥ ታስቦ መዘጋጀቷን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ለሳተላይቷ የተቀመጠላት ጊዜ አማካኝ የአገልግሎት ጊዜ እንጂ ሳተላይቷ ሁለት ዓመት ቢያልፋትም አሁንም ምስሎችን በመላክ ላይ መሆኗን ኢንጅነር መላኩ አክለዋል፡፡
የአንድ ሳተላይት አማካኝ የአገልግሎት ጊዜ ቢቀመጥም ብልሽት እና የጥራት ጉድለት ያሳዩ የተወሰኑ ክፍሎችን በማደስ እና ሌሎች መፍትሄዎችን በመውሰድ የአገልግሎት ጊዜን ማራዘም ይቻላልም ተብሏል፡፡
ከመሬት በ628 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለችው ይህች የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት በቀን በአማካኝ አራት ጊዜ ምስሎችን እየላከች መሆኗን ያነሱት ስራ አስፈጻሚው በተለይም ለግብርና፣ ለደን ልማት፣ የመሬት ቅርጽ ጥናት እና ሌሎች መረጃዎችን ለመንግስት እና ለግል ተቋማት እንዲደርስ መደረጉን ነግረውናል፡፡
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ አያያዝን ጨምሮ የከርሰ ምድር ውሃ መጠንን ለማወቅ፣ የመሬት ላይ ሽፋን እና ለተለያዩ ጥናትና እና ምርምር ስራዎች የሚያግዙ ምስላዊ መረጃዎችን ከዚች ሳተላይት ማግኘቷ ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ይህችን ሳተላይት በማምጠቋ የእውቀት ሽግግር እንዲፈጠር ከማድረግ አንጻር ብዙ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ልምዶች መገኘታቸውንም ኢንጅነር መላኩ ተናግረዋል፡፡
የስፔስ ሳይንስ ሙያን ለማጥናት ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችን ከማሳደግ ጀምሮ ከሳተላይት የሚገኙ መረጃዎችን መተንተን መቻሉንም አክለዋል፡፡
ETRSS2 የተሰኘች ሳተላይትን ለማምጠቅ ዝግጅቶች በመገባደድ ላይ ናቸው የሚሉት ኢንጅነር መላኩ ሳተላይቷ ከዚህ በፊት ከነበሩት የተሻሉ መረጃዎችን ማግኘት ያስችላልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ወደ ህዋ ያመጠቀቻቸው የምስል መቀበያ ሳተላይቶች እንጦጦ ካለው የሳተላይት መቆጣጠሪያ ማዕከል ካሉ ባለሙያዎች ጋር የነበራት እለታዊ ግንኙነት አራት ጊዜ ብቻ የነበረ ሲሆን በቀጣይ ግን ድግግሞሹን ከፍ ለማድረግ መታሰቡ ተገልጿል፡፡
ETRSS2 ሳተላይት መቼ እና ከየት ትመጥቃለች? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ “የምትመጥቅበት ትክክለኛው ጊዜ እና ቦታ በቀጣይ ይፋ ይደረጋል” ሲሉ ኢንጅነር መላኩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በግዛቷ በሚያልፉ ዓለም አቀፍ ሳተላይቶች መረጃዎችን መቀበል እና ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ገጠማን እያካሄደች መሆኑን ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡
የመረጃ መቀበያ ማዕከሉ ከዚህ በፊት የተገነባ ሲሆን አሁን እየተከናወነ ያለው ስራ ከሌሎች ሳተላይቶች መረጃ መቀበል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ገጠማ ስራዎችን ማጠናቀቅ መሆኑንም ኢንጅነር መላኩ አክለዋል፡፡
ይህ ተግባር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚያልፉ የሌላ ሀገራት እና ተቋማት ንብረት የሆኑ ሳተላይቶች በደቂቃ ተሰልቶ የሚገኝ ገቢ ሲሆን ከሳተላይቶቹ ባለቤቶች ጋር በመተባበር እና መረጃዎችን በመቀበል አገልግሎቱን ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እና ተቋማት በክፍያ ለመስጠት መታቀዱን ሰምተናል፡፡
በእንጦጦ ሳተላይት መቆጣጠሪያ ማዕከል የተገነባው ይህ መረጃ መቀበያ ማዕከል ምስሎችን በ7 ነጥብ 3 ዲያሜትር ርቀት ላይ በማንሳት ጥራት ያላቸውን መረጃዎች ለመንግስት ተቋማት በነጻ ለግል ተቋማት ደግሞ በክፍያ እያገኙ መሆኑንም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የጠፈር ሳይንስ ባለሙያዎችን እጥረት ለመፍታት ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የሁለተኛ እና ሶስተኛ ድግሪ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ትገኛለች ተብሏል፡፡