ሳተላይቷ ምን እንደገጠማት በተለያዩ አካላት ምርመራ እንደሚደረግ ተነግሯል
ብሪታንያ ሳተላይት ወደ ህዋ በማምጠቅ የመጀመሪያዋ የአውሮፓ ሀገር ለመሆን ያደረገችው ሙከራ አልተሳካላትም።
ሳተላይቷ ወደ ምህዋር እንዳትደርስ ያደረጋት ችግር እንደገጠማት ተነግሯል።
የ"አግድም ማስጀመሪያ" በተባለው ተልዐኮ በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ ከምትገኘው ከኒውኳይ የባህር ዳርቻ ከተማ ተነስታ የነበረችውና የቨርጂን ኦርቢት ሳተላይት በገጠማት ችግር ህዋ መድረስ አልቻለችም።
"ምህዋር ላይ እንዳንደርስ የከለከለን ያልተለመደ ችግር ይመስላል" ሲል ኩባንያው ተናግሯል። መረጃውንም እየገመገምን ነው ብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም የጠፈር ኤጀንሲ የንግድ ጠፈር ዳይሬክተር ማት አርከር "በሚቀጥሉት ቀናት በመንግስትና ቨርጂን ኦርቢትን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ምርመራ ይደረጋል" ብለዋል።
የተልዕኮው ክሽፈት ለአውሮፓ የጠፈር ምኞቶች የበለጠ ጉዳት ያስከትላል ተብሏል። በታህሳስ መጨረሻ ላይ ከፈረንሳይ ጊያና የተነሳ በጣሊያን የተሰራ የቪጋ-ሲ የተባለ ሮኬት አለመሳካቱን ሮይተርስ አስታውሷል።
አውሮፓ ባለፈው ዓመት ተከታታይ ሙከራዎች ውድቀት ገጥሟቸዋል ተብሏል።
የብሪታኒያ ቢሊየነር በሆኑት ሪቻርድ ብራንሰን በከፊል ባለቤትነት የተያዘው ቨርጂን ኦርቢት ከአሜሪካ ውጭ በጀመረው የመጀመሪያ ተልዕኮ ዘጠኝ ትናንሽ ሳተላይቶችን ወደ ምህዋር ለማሰማራት አቅዶ ነበር።