አረብ ኢሚሬትስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በንግድና ኢንቬስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ እንደምትሰራ አስታወቀች
አቶ ደመቀ መኮንን ከአረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላሂ ቢን ዛይድ ጋር ተወያይተዋል
አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርኪዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶጉሉ ጋርም በአቡዳቢ ተወያይተዋል
አረብ ኢሚሬትስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በሚመጥን መልኩ የንግድና ኢንቬስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ እንደምትሰራ አስታወቀች።
የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ ጋር በአቡዳቢ ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ውይይታቸውም በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ እና በሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
በውይይታቸው አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት መካከል በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ስለተፈረመው ስምምነት ገለፃ አድርገውላቸዋል።
ስምምነቱን ወደ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ያረጋገጡት አቶ ደመቀ፤ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እያደረጉ ላሉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በተጨማሪም በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ እና የአረብ ኤምሬትስ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር ይበልጥ ደግሞ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በኢትዮጵያ በኩል እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች ክቡር አቶ ደመቀ አብራርተዋል።
የአረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ በበኩላቸው በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ልዩ መሆኑን የገለፁት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግንኙነቱን በሚመጠን ደረጃ የንግድ እና ኢንቬስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርኪዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶጉሉ ጋር በአቡዳቢ ተወያይተዋል።
በውይይታቸው በዋናነትም ባሳለፍነው ሳምንት በኘሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት መካከል ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ገለፃ አድርገውላቸዋል።
ኢትዮጵያ እና ቱርክ ዘመንን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሃገራት መሆናቸውን በውይይቱ ላይ የጠቀሱት አቶ ደመቀ በአሁኑ ወቅትም ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ ተግባራት በተለያዩ መስኮች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውሰዋል።
የቱርክዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ሜቭሉት ካቩሶጉሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት በውይይት ለመፍታት የሰላም ስምምነት በመፈረሙ የቱርክዬ መንግስት የተሰማውን ደስታ ገለፀዋል።
ቱርክዬ በሁሉም መስክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።