ከነገ መጋቢት 20 ጀምሮ ማስክ የማያደርጉ ሰዎች ተጠያቂ እንደሚደረጉ ተገለፀ
ማንኛውም ሰው ከቤት ውጪ ያለ ማስክ መንቀሳቀስ እንዲሁም በእጅ መጨባበጥ የተከለከለ ነው
መመሪያውን የሚተላለፍ አካል በወንጀል ተጠያቂ ይሆናል
ከነገ ሰኞ መጋቢት 20/ 2013 ዓ.ም ጀምሮ የኮሮናቫ ቫይረስ መከላከያዎችን የማይተገብሩ ግለሰቦች እና ተቋማ በወንጀል ተጠያቂ ሊደረጉ ነው
ኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ስርጭቱን ለመግታት የሚያግዝ መመሪያ ቁጥር 30 መስከረም 25/ 2013 ዓ.ም የወጣ ቢሆንም አተገባበሩ ላይ ከፍተኛ ክፍተት ሲስተዋል ቆይቷል።
የጤና ሚኒስቴር፣ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ የኮቪድ 19 ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ በመመሪያ ቁጥር 30 የተቀመጡትን የክልከላ እርምጃዎች ተከታትሎ ማስፈፀም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት ከነገ ሰኞ መጋቢት 20/ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በመመረያው የተቀመጡ የክልከላ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የተለያዩ ክልከላዎችና ግዴታዎችን በግለሰብና በተቋማት ላይ የጣለው መመሪያው በሁሉም የሀገሪቷ ክፍሎች የሚተገበር ሲሆን፤ መመሪያውን የሚተላለፍ አካል በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆንም ተመልክቷል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በዛሬው እለት በፌስቡክ ገጻቸው ባጋሩት መረጃም፥ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች መመሪያው ላይ በተቀመጠው መስፈርት ስለመሆኑ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል፤ በሚመለከታቸው አካላትም አስፈላጊዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
በመመሪያው የተደነገጉ ክልከላዎች እና ግዴታዎች
ማንኛውም ሰው ለሰላምታና ሌላ ለማንኛውም አላማ በእጅ መጨባበጥ፤ ሆነ ብሎ የእርስ በእርስ አካላዊ ንክኪ ማድረግ የተከለከለ ነው
ማንኛውም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ቀሪ መሆኑ እስከሚወሰንበት ጊዜ ድረስ ከመኖርያ ቤት ውጪ በማንኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርግ መገኘት ወይም መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፣
ሆኖም ዕድሜያቸው ከ6 ዓመት በታች የሆነ ህጻናት ወይም በማሰረጃ የተረጋገጠ የመተንፈሻ አካላት ወይም መሰል ችግር ያለባቸው ሰዎች ይህ ድንጋጌ ተፈፃሚ አይሆንባቸውም፣
ማንኛውም የንግድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ቀሪ መሆኑ ካልተወሰነ በስተቀር አፍና አፍንጫውን ላልሸፈነ ሰው አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፣
ማንኛውም ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ቫይረሱ እንዳለበት እያወቀ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት፣ ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀል ወይም ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ በሚችልበት ሁኔታ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት የተከለከለ ነው፣
ስብሰባን በተመለከተ 50 ሰው በላይ መሰብሰብ ግዴታ ሆኖ ከተገኘ ስብሰባው ሊደረግበት የታሰበበት አዳራሽን ጠቅላላ ስፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቦታው ሊይዝ ከሚችለው ሰው ብዛት አንድ አራተኛውን በማይበልጥ ሰው ለሰላም ሚኒስቴር እና በተዋረድ ባሉ የክልል፣ ዞን እና ወረዳ የሰላም እና ፀጥታ መዋቅሮች አስቀድሞ በማሳወቅ ሊከናወን ይችላል።
የቀብር ሥነ-ሥርዓትን በተመለከተ ከ50 ሰው የበለጠ ሰው መገኘት እንደሌለበትና አስክሬን በጥንቃቄ መገነዝ እንዳለበትም በመመሪያው ተካቷል።
የተደነገጉ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው በወንጀል ህግ አንቀጽ መሰረት የሚቀጣ ይሆናል።