ኮቫክስ በዓለም ለ32 ሚሊዮን ዜጎች የኮሮና ክትባት ማቅረቡን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ
ድርጅቱ 20 የዓለማችን ሀገራት ክትባቱ ሳይደርሳቸው እንዳይቀር በስጋት ላይ መሆኑን ገልጿል
የ100 ቀናት ክትባት ማቅረቢያው ጊዜ ሳያልፍ ተጨማሪ ክትባቶች በሚቀጥለው 15 ቀናት ይከፋፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል
ኮቫክስ የተባለው የዓለም ጤና ድርጅት ማእቀፍ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 32 ሚሊዮን ክትባቶችን በመላው አለም ለሚገኙ 61 ሀገራት መከፋፈሉን አስታውቋል፤ የ100 ቀናት ክትባት ማቅረቢያው ጊዜ ሳያልፍ ተጨማሪ ክትባቶች በሚቀጥለው 15 ቀናት ይከፋፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት ክትባቱን እየሰጡ ካሉ 61 ሀገራት በተጨማሪ 36 ሀገራት ለመጀመሪያ ጊዜ ክትባቱን ለመስጠት በሂደት ላይ መሆናቸውንም ድርጅቱ በሪፖርቱ ላይ ጠቁሟል።
ኮቫክስ ክትባትን ለ16 ሀገራት ለማዳረስ እየሰራ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ 20 የዓለማችን ሀገራት ክትባቱ ሳይደርሳቸው እንዳይቀር በስጋት ላይ መሆኑንም አስታውቋል።
አሁን ላይ 10 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት እንደሚያስፈልገው የተናገረው ድርጅቱ አቅም ያላቸው ሀገራት ለድርጅቱ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።
የኮቫክስ ክትባት በመላው አህጉር በመሰጠት ላይ ቢሆንም ብዙ አገራት በሶስተኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ክፉኛ መጠቃት ጀምረዋል። ብዙ ሀገራትም ስርጭቱን ለመከላከል ጥብቅ እርምጃዎችን በመውሰድ ላየ ይገኛሉ።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን በዓለማችን በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ዜጎች ቁጥር ከ126 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን እንዳጡ የጆን ሆፕኪንስ ዩንቨርሲቲ መረጃ ይጠቁማል።
በአፍሪካ ደግሞ 4.2 ሚሊዮን ዜጎች በኮሮና ቫይረስ ሲጠቁ ከ111 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ በዚህ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን እንዳጡ የአፍሪካ በሽያ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል ገልጿል።
በአጠቃላይ አፍሪካ ለ40 ሚሊዮን ዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ስታደርግ ከ25 በላይ የአህጉሪቱ አገራት ኮቫክስ የተሰኘውን ክትባት ለዜጎቻቸው በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
የኮሮና ቫይረስ የስርጭት መጠን በአፍሪካ 10 በመቶ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን ከ20 በመቶ በላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያስረዳል።