ሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ዘመቻ ተጀመረ
በቀጣይ 2 ሳምንታት በየቀኑ እስከ 6 በሚደርሱ በረራዎች 40 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ እየተሰራ ነው
በዛሬው ዕለትም ከ2 ሺህ በላይ ስደተኞችን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ተጀምሯል- በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ
በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያንን በወደ ሀገር ቤት የመመለስ ዘመቻ በዛሬው እለት መጀመሩን በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።
በህገ ወጥ መንገድ የሳዑዲ አረቢያን ድንበር ጥሰው የገቡ እንዲሁም የሳዑዲ የመኖርያና የሥራ ፈቃድ ህግጋትን ተላልፈው በመገኘታቸው ከአንድ አመት በላይ በእስር የቆዩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይታወቃል።
በቅርቡ መንግስት እነዚህ እስረኞች በሙሉ ወደ አገር እንዲገቡ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ ብዛት ያላቸው በረራዎች ከሳዑዲ ወገን ጋር በመነጋገር የሚመቻቹ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቋል።
ይህን ለማሳካት የሁለቱ አገራት መንግስታት ባደረጉት ስምምነት መሰረት ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቋሞ ዜጎችን በስፋት ወደ አገር የመመለስ ሂደት ለማሳካት ከኢትዮጵያ ወገን ቀዳሚ ልዑክ ቡድን ተልኮ ከሳዑዲ አረቢያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ጥልቅ ውይይት በማድረግ ዜጎችን የማስመለስ ስራ መመቻቸቱንም ገልጿል።
በዚሁ መሰረት ከሰኔ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በየቀኑ እስከ ስድስት በሚደርሱ የሳዑዲና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች በማቆያ ጣብያዎች የነበሩ ዜጎች የሚመለሱ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲም በተለያ ማእከላት ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮፕያውያንን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ስራ መጀመሩን አስታውቋል።
በዛሬው እለት ከ2 ሺህ በላይ ስደተኞችን ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ የተባለ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት 6 በረራዎች በማድርግ ዜጎች ለአሀራቸው እንዲበቁ ማድርግ መጀመሩን ኤምባሲው አስታውቋል።
በዚህ የማስመለስ ሥራ ቅድሚያ ወደ አገር እንዲገቡ የተደረጉት ሴቶች፣ ህጻናት እና ታማሚ ዜጎች መሆናቸውንም ነው የገለጸው።
መንግስት ከሳኡዲ አረቢያ መንግስት ጋር በመሆን በተለያዩ ማቆያ ማእከላት ውስጥ የሚገኙ 40 ሺህ ኢትዮፕያውያንን በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በተከታታይ ወደ አገር እንደሚመልስም ኤምባሲው አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳላፍነው ሀሙስ በሰጡት መግለጫ የሚሳካ ከሆነ በሁለት ሳምንታት ውስጥ በሳዑዲ ያሉ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ መግለጻቸው ይታወሳል።
በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እንግልትና ስቃይ እየደረሰ መሆኑን ሚኒስቴሩ መረጃዎች እንደደረሱት ያነሱት አምባሳደር ዲና ይህንን ለማስቆምና የዜጎችን ክብር ለማስጠበቅ ኮሚቴው እየሰራ መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል።