ሳዑዲ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ (ኢቃማ) በትንሹ ከ3 ባልበለጡ ወራት ውስጥ እንዲታደስ ወሰነች
ኢትዮጵያ ብዙሃኑን ከሳዑዲ ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗ ይታወሳል
ውሳኔው በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሃገሪቱ የገቡ በርካታ ኢትዮጵያውንን እንደሚነካ ይታሰባል
የሳዑዲ አረቢያ ካቢኔ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ (ኢቃማ) በትንሹ ከሶስት ባልበለጡ ወራት ውስጥ መታደስ አለበት በሚል የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ አጸደቀ፡፡
ውሳኔው የቤት ሰራተኞችን እና ተያያዥ የሙያ ዘርፎችን የማይመለከት ነው ተብሏል፡፡
የመኖሪያ እና የስራ ፈቃዶች የማሳደሻ ክፍያ ተከፋፍሎ የሚፈጸም ነው የተባለ ሲሆን የሚሰጥበትን እና የሚታደስበትን ጊዜ ታሳቢ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
ካቢኔው በተጨማሪ በሪያድ የሚገኘውን የዲፕሎማሲ ባለስልጣን መስሪያ ቤትን ከእነ ሙሉ አደረጃጀቱ ያፈረሰ ሲሆን ሙሉ ተልዕኮዎቹ፣ ጅምር ስራዎቹ፣ በጀት እና ሰራተኞቹ ጭምር ወደ ሪያድ ንጉሳዊ ኮሚሽን (Royal Commission for Riyadh) እንዲዛወሩ አዟል፡፡
የውሳኔ ሃሳቡ የጸደቀው ከትናንት በስቲያ በንጉስ ሰልማን ሰብሳቢነት በተካሄደው ቨርቹዋል የካቢኔ ስብሰባ ነው፡፡
በሳዑዲ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ናቸው፡፡ የስራ እና የመኖሪያ ፈቃድ (ኢቃማ) ያላቸው ቢኖሩም አብዛኞቹ ኢቃማ የሌላቸው በህገ ወጥ መንገድ በባህርም አና በሌሎችም መንገዶች አቆራርጠው ሳዑዲ የገቡ ናቸው፡፡
ቁጥራቸው ምናልባትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሊቀንስ ቢችልም ከአንድ መቶ ሺ ሊበልጥ እንደሚችሉ ይነገራል፡፡
በመሆኑም ውሳኔው በአንድም በሌላም መንገድ እንደሚነካቸው ይታሰባል፡፡
ኢትዮጵያ ይህን ችግር በመቅረፍ የዜጎቿ መብት እንዲከበር ለማድረግ ከሚመለከታቸው የሃገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር እየሰራች ነው፡፡
የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ወደ ሃገራቸው ለመመለስም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ትናንት ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ብቻ 293 ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ገለጻ።
በየቀኑ ወደ ሃራቸው የሚመለሱትን ዜጎች ቁጥር ከፍ ለማድረግ መታሰቡም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለማድረግ መወስኗ ይታወሳል፡፡