“ከተሳካ በ2 ሳምንት ውስጥ ሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያውያንን እንመልሳለን”- አምባሳደር ዲና
ወደ ሳዑዲ ያመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር ተወያይቷል
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ሱዳን የተመድ ጸጥታው ም/ቤት በግድቡ ዙሪያ ይወያይ ስትል “አፍሪካ ሕብረት ምን አደረገሽ? ማለት እንፈልጋለን” ብሏል
በሳዑዲ አረቢያ ችግር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገራቸው እንደሚመልስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የሚሳካ ከሆነ በሁለት ሳምንታት ውስጥ በሳዑዲ ያሉ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ገልጸዋል፡፡
ዜጎቹን ለመመለስና ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር ለመነጋር የሚያስችል ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሳዑዲ ማቅናቱን የገለጹት ቃል አቀባዩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዜጎቹ እንደሚመለሱ አስታውቀዋል፡፡
በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እንግልትና ስቃይ እየደረሰ መሆኑን ሚኒስቴሩ መረጃዎች እንደደረሱት ያነሱት አምባሳደር ዲና ይህንን ለማስቆምና የዜጎችን ክብር ለማስጠበቅ ኮሚቴው እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ በሚኒስቴሩ የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ መስፍን ሻዎ የተመራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲን ጨምሮ ቡድኑ በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች መብትና ደህንነት በሚከበርበት እና ወደ አገር በሚመለሱ ዜጎች ዙሪያ ከሳዑዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ተሚሚ አል-ደውሰሪ እና ከሳኡዲ አረቢያ የአገር ግዛት ሚኒስቴር ልዩ የደህንነት አማካሪ ጄኔራል ጀምዓን አዛህራኒ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
በዚህም መሰረት የሳኡዲ አረቢያን የድንበር ደህንነት ሥርዓት ጥሰው የገቡ፣ የአገሪቱን የመኖሪያ ፍቃድ እና የሥራ ፈቃድ ሕግጋትን ተላለፈው የሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆና በገዛ ፍቃዳቸው በተፋጠነ ሁኔታ እና በሁለቱ አገራት መንግስታት የጋራ ትብብር ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደት በቅርብ ቀን እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡
የልዑካን ቡድኑ፤ በጂዳ ሹመይሲ እስር ቤት ጉብኝት በማድረግ ኢትዮጵያውያን ታራሚዎች ያሉበትን ሁኔታ ማየቱንና ማነጋገሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ኢትዮጵያ እና ሱዳን
ሱዳን፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ም/ቤት በግድቡ ጉዳይ እንዲሰበሰብ ጥያቄ ማቅረቧን በተመለከተ የተጠየቁት አምባሳደር ዲና፤ “አፍሪካ ሕብረት ምን አደረጋችሁ? ለምን ባህር ማዶ ትሄዳላችሁ? ነው መልሳችን” ሲሉ መልሰዋል፡፡
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም ሳዲቅ አል-ማህዲ የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ግድቡ “በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ደህንነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ” ለመወያየት በተቻለ ፍጥነት ስብሰባ እንዲያካሂድ ጥሪ ማቅረባቸው የተገለጸ ቢሆንም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ግን ጥያቄው ተገቢ ያልሆነና ለአፍሪካ ክብር የማይሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሱዳን በአብዬ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲወጣላት ጥያቄ ስለማቅረቧ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እየተገለጸ ነው፡፡
አምባሳደር ዲና ሰላም አስከባሪ የማስገባትና የማስወጣት ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊነት እንጅ የሌላ አካል አለመሆኑን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡