መርህ ተጥሷል ለሚሉት ግብጽ እና ሱዳን“በይፋዊ ደብዳቤ መልስ ይሰጣቸዋል”-የውሃ እና ኢነርጅ ሚኒስትር
ግድቡ ከሁለት ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ ይጠናቃል ብሏል ሚኒስቴሩ
ኢትዮጵያ፣ግብጽ እና ሱዳን የጀመሩት የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር ሂደት ምን ደረጃ ላይ ነው?
በኢትዮጵያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋን (ዶ/ር) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡ሚኒስትሩ፤ ወደ ውኃና ኢነርጅ መስሪያ ቤት ከመምጣታቸው አስቀድሞ በመምህርነት እና በኦሮሚያ ክልል ውኃና ኢነርጅ ቢሮ ኃላፊነት በመሆን አግልግለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በአንዱ ተርባይን ኃይል ማመንጨት ከጀመረ በኋላ አል ዐይን አማርኛ ከሚኒስትሩ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ጋር ያደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ እንድትከታተሉ በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የሕዳሴ ግድብ አንድ ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀምሯል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር) ፡- የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ጉልበት፤ በራሳቸውን ገንዘብ ሳይተርፋቸው ነገ ለሀገር ያስፈልጋል ብለው በአቅማቸው ልክ እያዋጡ እያለሙት ያለ ፕሮጀክት ነው፤ ያ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክትና አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት የዛሬ 10 ዓመት አካባቢ ሲጀመር ኢትዮጵያውያን ማድረግ እንደሚችሉ ጉዞ የጀመሩባቸው ስራዎች ፤ የራሱ መንገራገጭ ቢኖረውም በተለይ ከአዲሱ ለውጥ በኋላ ማስተካከያዎች ተደርገው በተሳካ ሁኔታ ለኢትዮጵያውያን የመስራች ፍሬ ማየት ችለናል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ቀጣዩ ተርባይን መቸ ነው ስራ የሚጀምረው?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር) ፡- ጠቅላላ ግድቡ 13 ዩኒቶች አሉት፤ ከዛ ውስጥ ሁለቱ ዩኒት 9 እና 10 ቅድሚያ ወደ ስራ የሚገቡ ናቸው፤ ቴክኒካሊ ተርባይኖች ኃይል የሚያመነጩት ውኃው እዛ በሚደርስበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለቱ ከታች ያሉ በአንድ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አላቸው፡፡ ዩኒት 10 አሁን ሙሉ ለሙሉ ፍተሻው አልፎ በተሳካ ሁኔታ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ነው፡፡ አንደኛው ደግሞ በዛው ልክ ወደ ማለቅ እየደረሰ ነው ያለው፡፡ የተወሰኑ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች አልቀ ወደ ፍተሻ ስራ ውስጥ የሚገባ ይሆናል፡፡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በጨረስንበት ጊዜ በበቂ ሁኔታ የሚፈለገውን የውኃ መጠን ስለያዝን ኃይል የማመንጨት አቅም አለን፤ አጎልብተናል፡፡ ከዛ በኋላ ሲቪል ስራዎቹ ናቸው የሚቀጥሉት፡፡ ስራዎቹ ሲቀጥሉ ወደ ላይ የቀሩት 11 ተርባይኖች ደግሞ ውኃ ሲደርስላቸው ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ሁለተኛው ተርባይን ማለትም ዩኒት 9 መቸ ኃይል ሊያመነጭ ይችላል?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር) ፡- ይጀምራል፤ ባለፈውም ስንናገር እንደነበረው ሰዎች ዩኒት 10 መቸ ነው የሚጀምረው? በሚሉበት ሰዓት እኛ በቅርቡ ጨርሰን ሕዝባችንን የምስራች እንላለን እንዳልነው ሁሉ እሱም በዛው ልክ (ዩኒት 9 ማለት ነው) ሰርፕራይዝ ነው የምናደርገው ፡፡ ወደኋላ ሄደን ታሪካችንን ብናይ የመጀመሪያ ዙር ውኃ ሙሌት ከተጠበቀው ጊዜ ቀደም ብሎ ነው የተደረገው፤ ሁለተኛው ዙርም በዛው ልክ፤የመጀመሪየው ዙር ኃይል ማመንጨትም በዛው ልክ ነው ለኢትዮጵያውያን የተነገረው፤ ይሄ ትርጉም ስላለው ነው ለኢትዮጵያውያን፡፡ አንደኛ ኢትዮጵያውያን ከውስጥ ሆነው በትዕግስት የሚጠብቁትና መቸ ፍሬውን ላግኝ? የሚል ነገር አላቸው፤ በዛው ልክ ደግሞ እኛን የሚገዳደሩና ልማታችንን የማይፈልጉ ይህንን ለማደናቀፍ የሚሰሯቸው ስራዎች ስላሉ በዛ በኩል ታሳቢ ተደርጎ ነው ስራዎች የሚሰሩት፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያ ኃይል ያመነጨችበት መንገድ በፈረንጆቹ 2015 ላይ ካርቱም ላይ የተደረገው የመርሆዎች ስምምነት ይጥሳል እያሉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምላሽ ምንድነው?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ሲጀመር 2015 ላይ ካርቱም ላይ የተደረገው የመርሆች ስምምነት አብሮ የመስራት ነው፡፡ ከእሱ ይልቅ ወሳኙ ሲኤፍ ኤ (ኮምፕሪሄንሲቭ ፍሬም ዎርክ አግሪመንት) ነው፡፡ ግብፅ እና ሱዳን ይህንን አንፈርምም ብለው በጣም እያስቸገሩ ያሉበት ትልቁ ሰነድ እሱ ነው፤ አሳሪ ሊያደርግ የሚችል ጭምር ማለት ነው፡፡ የመርሆች ስምምነት ላይ ምንም የሚያስገድድ ነገርም የለም፤ ከዚህ ጋር የተገናኘ ነገርም የለውም፡፡ ሲጀመር ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ነች፤ የራሷን ሀብት የመጠቀም መብት ያላት ሀገር መሆኗንም ጭምር መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ የመርሆች ስምምነት ከተነሳ አይቀር ያ ጉዳይ የሚመለከተው ቀሪውን የናይል ተፋሰስ ሀገራትን ማለትም በነጭም፣ በብሉና ናይልም እስከ ሜዲትራኒያን ጭምር ያለው ነው፡፡ ለምሳሌ ግብፆችን ብናይ ይሄ ድርድር ከተጀመረ ወዲህ ራሱ ወደ ስምንት ፕሮጀክቶችን ጀምረዋል፤ ያውም ግብርና ነክ፤ ውኃን የሚጠቀምና ሊያባክን የሚችል የውኃ ፕሮጀክቶችን እየሰሩ ነው ያሉት፡፡ ስለሱ ጉዳይ እኛ መቸ ተናገርን? ስለሱ አጀንዳ ኢትዮጵያውን መቸ አነሳን? እዛ ያለውን ነገር መጠቀም ይችላሉ፤ እዛ ያለውን ባላንስ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ አሁን ከምታደርገው ኃይል ማመንጨት ጋር የመርሆች ስምምነት ጉዳይ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ከዚህ በነበረው የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት ጊዜም ይህንን አቋም ያራምዱ ነበር፡፡ የአንድ ወገን ውሳኔ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የውኃ ተቋም የምናለማቸው ማንኛውም ፕሮጀክት የውኃ መጠኑን እስካልነካን ድረስ ለመጠቀም የነሱ ቡራኬ አያስፈልገንም፡፡ እንደዛ የሚያስገድድ ሕግም የለንም እንደ ሀገር፡፡ ስለዚህ የተሳሳተ መረጃ ነው በራሳቸው ጊዜ እንዲሁ ለማጣጣል ያህል የሚያደርጓቸው ሙከራዎች ናቸው እንጅ ሕጋዊ መሰረት የላቸውም፡፡ ለሚያነሷቸውም ደግሞ ተገቢ መልስ እየሰጠን እንገኛለን ማለት ነው፡፡
አል- ዐይን አማርኛ፡- ስለዚህ ኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ስራ መጀመሯ የትኛውንም ሕግ አይጥስም ማለት ነው?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር) ፡- የመርሆዎች ስምምነት ላይም እንደዛ የለውም፤ ስለዚህ እነሱ በወቅቱ ይህ ዜና ሲመጣባቸው እንደ ምክንያት ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ የሚመጣው ለውጥ እንደሌለ እርግጠኞች ነን፡፡
አል- ዐይን አማርኛ፡- አንዱ ተርባይነ 375 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ነው የጀመረው ተብሏል፡፡ ግብፅ ደግሞ በ 150 ሜጋ ዋት ነው የተጀመረው እያለች ነው፡፡ ትክክለኛው ቁጥር የትኛው ነው?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር) ፡- የነሱ ስራ አንድ በተቻለ መጠን ስራ እንዳይሰራ የማድረግ ስራ ነው፤ ከዛ አልፎ ደግሞ መሳካቱን ሲያዩ ማጣጣል ነው፡፡ ስለግድባችን የምናውቀው እኛ ነን፡፡ የተርባይኑን መጠን የምናውቅ እኛ ነን፤ የውኃውን ከፍታ የምናውቅ እኛ ነን፤ ስለዚህ እንዲሁ መሸነፋቸውን ለማካካስ የሚያደርጉት አሉባልታ ካልሆነ በስተቀር እኛ ሙሉ አቅም ማለትም 375 ነው የምናመነጨው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ኢትዮጵያ ሁለት ዙር የውኃ ሙሌት አካሂዳለች፡፡ የፊታችን ክረምት ላይ ሶስተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በመርሃ ግብሩ መሰረት ይከናወናል?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- አዎ፤ ምክንያቱም የእኛ ግድብ አካሄዱ ራሱ ከስር እየገነባን ስንሄድ ውኃ መያዙ የተፈጥሮ ነው የሚሆነው ማለት ነው፡፡ በተለይ ባለፉት የተወሰኑ ወራት ትልቁን ጊዜ የወሰደው በእርግጥ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው ላይ ነው፡፡ በእሱ ላይ ጊዜ ተወስዷል፤ በሀገር ውስጥ የተፈጠረው የተወሰነ የሲሚንቶ እጥረትም እንዳለ ቢሆንም ግንባታው እየቀጠለ ነው ያለው፡፡ ግንባታው በሄደው ልክ ግድባችንም እየሞላ ይሄዳል፤ የፊታችን ክረምትም ሶስተኛው ዙር ውኃ ሙሌትን እንቀጥላለን፡፡ በወዲያኛውም ሙሊቱ ማንም ሊያስቆም በማይችልበት ሁኔታ በየዓመቱ እየሞላ ይሄዳል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ሶስተኛውን ዙር ሙሌት ለማድረግ የሚቀረው ስራ ምንድነው?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ከኃይል ማመንጨት በኋላ የቀረን በጣም ወሳኙና ትልቁ ስራ የሲቪል ስራ ነው፡፡የግድቡን ከፍታ መጨመር ፤ በሁለቱም ዊንግ ላይ ያለው ከፍታ በጣም ሄዷል፤ በመካከል ላይ ያለውን በምናይበት ሰዓት ውኃው የሚፈስበት ቦታ ላይ ከሱ ከፍ ማለት የሚጠይቁ ስራዎች አሉ፤ ያንን እየሰራን ነው ያለነው፡፡ ያንን ከፍ እያደረግን በሄድን ቁጥር ሙሌቱም በዛው ልክ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ አንድ መገንዘብ የሚገባን ነገር እኛ ሙሌቱን ስናደርግ በታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ላይ የሚያመጣው ጉዳት የለም፡፡ ምክንያቱም ውኃውን ከሞላን በኋላ (እነርሱ ጋር ቢሄድ ጎርፍ ያስቸግራል) ባለፈው የተመረቀው የመጀመሪያው ዙር ዩኒት 10 ላይ ያለው ሃይድሮ ፓወር ጀነሬተር ካለፈ በኋላ ወደ ፍሰት ገብቶ ነው የሚቀጥለው፡፡ ስለዚህ እየሞላን ስንሄድ ግድቡን ከፍ ባደረግን ቁጥር ሙሌቱ ይቀጥላል፡፡የግድቡን ከፍታ የመጨመር ስራ ነው ዋናው፤ ለዛ ደግሞ ሕዝቡን ማነሳሳት ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው ተርባይ ዩኒት ዘጠኝ የሚጠናቀቁ ስራዎች አሉ እነሱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የሶስትዮሽ ድርድሩን በተመለከተ ከአደራዳሪው የአፍሪካ ሕብረት አዲሱ ሊቀመንበር የደረሳችሁ ጥሪ አለ? ከኃይል ማመንጨት በኋላስ የተቀየረ አቋም አላት?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ ያላት አቋም የጋራ ተጠቃሚነት ነው፡፡ አጎራባች ሀገራት ለእኛ ወገኖቻችን ናቸው፤ በቀጣናው ያሉት ከኢትዮጵያውያን ጋር ተደምረው በጋራ ማደግ ነው የምንፈልገው እንጅ ኢትዮጵያ ለብቻዋ ተነጥላ ለራሷ ብቻ ተጠቃሚነት የሚል አቋምም የለንም፤ ኖሮን አያቅም፤ ወደፊትም ሊኖር አይችልም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ስንነሳ ድርድሩን በማንኛውም ጊዜ አጀንዳው ሲመጣ ኢትዮጵያ ለማስተናገድ ዝግጁ ናት፡፡ እውነት ነው ባለፈው የተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ነበር፤ አንዱ ምክንያት ሱዳን ላይ የተፈጠረው አለመረጋጋት ሲሆን ለባለፈው አንድ ዓመት ይህንን ጉዳይ ዴሞክራቲክ ኮንጎም ብዙ ነገሮችን ቢሰሩም በሚፈለገው ደረጃ ሊሄድ አልቻለም ነበር፡፡ ምክንያቱም የታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ፍላጎት ይወስናል፡፡ አሁን ሴኔጋል የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ሆናለች፡፡ እና አሁን እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እንደሀገር ያን ድርድር በማንኛውም ነገር እንደግፋለን፤ መቀጠልም አለበት ማለት ነው፤ ምክንያቱም መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ በእኛ በኩል በፊት የነበረው አቋማችን እንደቀጠለ ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ ደግሞ ጥሪ ሲተላለፍም ለመሄድም ዝግጁ ነን፡፡ ሴኔጋል ሊቀመንበር የሆነችው በቅርቡ ነው እናም አጀንዳው አልተነሳም፤ አጀንዳው ሊነሳ የሚችለው ብዙ ጊዜ ወደ ሙሌቱ ስንጠጋ ነው፡፡ በዛው ልክ እኛ እንዘጋጅና ዲፕሎማሲውን በሚመለከት የናይል ቤዚን ኢኒሸቲቭ ተቋም ሲኖር ይህንን በበላይነት የምትደግፍ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ግብፅ በተቻለ መጠን እንዲፈርስ ሁሉ ያስባሉ፤ እኛ ግን መሆን የለበትም ተቋም ያስፈልጋል የሚል አቋም ስላለን እንሰራበታለን፡፡ ለምሳሌ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ሲከበር የነበረው የናይል ቀን መርሃ ግብር ነበር፡፡ በዛ ላይ የእኛ ልዑክም ተሳትፏል፤ እኛም በበይነ መረብ ከዚህ ተሳትፈናል፤ ሌሎቹ ሀገራት ሰውም አላኩም ፤ ምንም የባለቤትነት ስሜት በማይሰማው ሁኔታ ችላ የማለት ነገሮች ይታያሉ፡፡ በእኛ በኩል ያንን ትልቁን ስራ እየሰራን እንገኛለን፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ የገጠመ ችግር አለ?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- እንኳን ሕዳሴን የሚያክል ግዙፍ ግንባታ ይቅርና ማንኛውም ግንባታ ችግር ያጋጥመዋል፡፡ ከኮቪድ ጋር ባጋጠመ ዓለም አቀፍ ችግር ምክንያት ምርት ቶሎ አለማቅረብ፤ ከሲሚንቶ ጋር፣ ከብርት ጋር የተገናኙ የተወሰኑ ነገሮች ይኖራሉ፤ የሕዳሴ ግድብ ከዛ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሲሚንቶ ግብዓትና የውጭ ምንዛሬ በተለየ ሁኔታ በብሔራዊ ባንክ ተፈቅዶ ድጋፍ እየተደረገ ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ኢትዮጵያ ከዓባይ በተጨማሪ ሌሎች ወንዞች አሏት፡፡ እነሱ ላይ ፕሮጀክቶች ይጀመሩ ይሆን?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ የውኃ ሀብት አላት፡፡ ይሄ ተፋሰስ ከተፋሰስ ይለያያል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ውኃ በጣም ሞልቶ እንደሚትረፈረፍ አድርገው የውጭ ሚዲያዎች፤ ግብጾችም ጭምር ያወራሉ፡፡ ሃቁ እንደዛ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ ዓባይ ተፋሰስ ዝናብ ይኖረዋል እውነት ነው ወንዞች አሉ እውነት ነው፤ አዋሽ ተፋሰስን ወደ ምስራቅ በኩል ብናይ ድርቅ ያለበት ቦታ ነው፤ ክረምት ጎርፍ ይኖራል ፤ በበጋ ጊዜ ትልቅ እጥረት ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያን ብናይ ከፍተኛ እጥረት ውስጥ ነው ያለው፡፡ እንደሀገር በምናይበት ጊዜ ያለንን ውኃ ካለን የመሬት ስፋትና ሕዝብ ብዛት ጋር ስናይ እኛ አሁን ካለን በላይ ውኃ እንደሚያስፈልገን ማመን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ፍላጎቱ በዛ ልክ ካለና ሀብት ካለ ኢትዮጵያ ያንን ታለማለች፤ እየተጠቀመችበትም ትቀጥላለች ማለት ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ስለዚህ ሌሎች ፕሮጀክቶች ሊኖሩ ይችላሉ?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- አዎ ይኖራሉ፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ግድቡ መቸ ያልቃል?፤ ሁሉም ተርባይኖች ስራ የሚጀምሩት መቸ ነው?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር) ፡- ግድቡ ድሮ ስናስብ አምስት ዓመት የሚል ዕቅድ ነበር፤ በዛ ልክ አልሄደም፡፡ የመጀመሪያው ሰባት ዓመት በትልቅ ፈተና ነው የታለፈው የአመራር ችግር፣ የራስ ችግር ውጫዊና ውስጣዊ የሆኑ ጉዳዮች ነበር፡፡ ያ ተስተካክሎ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመት ውስት በጣም ፈጣን በሆነ ሁኔታ ነው እየተሰራ ያለው፤ ቁርጠኝነቱ በትልቁ አለ፤ በምክር ቤትም እየተነጋገርን ያለነው ይህ ልምድ በጣም ሊቀጥል እንደሚገባ ነው፡፡ ስለዚህ ከሁለት ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ ግድቡን እንጨርሳለን፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ስለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ምን ማለት ይፈልጋሉ?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- በሁለት መልኩ ነው የምናየው፡፡ ሌሎቹ ተፋሰስ ሀገራት ችግር የለባቸውም፤ ለምሳሌ አንዱ ተፋሰስ ሀገር ኮምፕሪሄንሲቭ ፍሬም ወርክ አግሪመንት እንዲፈረም ግፊት በማድረግ የእኛን አቋም አንጸባርቋል፡፡ የግብጽ በተለየ ሁኔታ በምናይበት ሰዓት ከመጀመሪያውኑ ጀምሮ የሚቃወሙ ወገኖች ናቸው፤ ይቀጥሉታል ብለን ነው የምናምነው እኛ ፡፡ ለነሱ ሁለት መልዕክት አለን፤ ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር ናት፤ የውኃ ሀብቱም ከዚች ሀገር ነው የሚነጨው፤ ሲመነጭም ዝም ብሎ ሳይሆን ዋጋ ተከፍሎበት ነው፤ ኢትዮጵያውያን መሬት ሰጥተው፤ ችግኝ ተክለው፤ ተንከባክበው የሚያለሙትን ውኃ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገሮች ሳይጎዱ የመስራት መብት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዛ አልፎ ደግሞ ስም የማጥፋት ስራዎች ተገቢ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ግብፅን ለመጉዳት እንደምትሰራ አድርገው የሚናገሩ ስራዎች ትክክል አለመሆናቸውን ሊረዱ ይገባል፡፡ የመርሆች ስምምነትን ኢትዮጵያ ጥሳለች ለሚሉትም እንደሀገር ተገቢውን መልስ እንሰጣለን፡፡ ይሄ ለምንድነው ለመግባባት፤ የተጻፈው ምን እንደሚል፤ መሬት ላይ ያለው ጉዳይና ሁኔታ ምን እንደሚመስል ዓለምም እንዲረዳው ለማድረግ ነው፤ ይህ የእኛ ስራ ይሆናል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- መልስ የሚሰጣቸው በምን መልኩ ነው?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ጥያቄ አላቸው፤ ለምሳሌ የመርሆዎች ስምምነትን ጥሳችኋል የሚል ነገር አላቸው፤ እኛ ደግሞ በዚህ፣ በዚህ ምክንያት አልጣስንም የሚል ያንን መልስ መስጠት ነው፡፡ አሁን ሰሞኑን በሚዲያ የሚያደርጉትን በይፋዊ ደብዳቤ መልስ ይሰጣቸዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ኢትዮጵያ አሁን ላይ ኃይል ትሸጣለች?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር) ፡- ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን ስትጠቀም የመጀመሪያው ስራችን እንደሀገር ለእኛ ብቻ የሚል ነገር የለንም፤ አንደኛው ምክንያት ጎረቤት ሀገራትን ይዘን መነሳት አለብን፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ለራሳችን የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ የተነሳ ባለፉት ዓመታት በቀጣናዊ ትስስር ሁኔታ ላይ ለጎረቤት ሀገራት ማለትም ከጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን ጋር የተጀመሩ ስራዎች አሉ፡፡ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የምናለማው ኃይል ለሀገር ቤት ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገሮችም ማድረስ ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ የውኃ ሃብቱ የሚሄድባቸው ሀገራት የመጠቀም መብትም ሊሰጣቸው ይገባል ከእኛ መነጨ ሃይል ቢጠቀሙ የጋራ ዕድገታችንን ያጎለብታል፡፡ እነሱ የማይችሉትን ሃብት ይጠቀሙበታል፤ ለምሳሌ ሱዳን ለሃይድሮ ፓወር አይመችም፤ ለመስኖ ነው የሚመቸው ፡፡ ስለዚህ እኛ ኢነርጅ ብንሰጣቸው እነሱ የግብርና ምርት አምርተው ብንጠቀም አብሮ ለማደግ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡ እኛ የምናምነው በዚህ ነው፡፡ ከሱዳን ጋር፣ ከኬንያ ጋር፣ ከጅቡቲ ጋርም በዛው ልክ ሲሆን ለቀጣናዊ ትስስርና ትብብር መሰረት ነው፡፡ ለዚህም ትልቁ ዕድላችን ኢነርጅ ነው፡፡ ይሄ ኢነርጅ ደግሞ አሁን የምናመነጨው ፓወርን መሰረት አድርጎ ነው የሚሄደው፤ የተጀመሩ ስራዎች አሉ፤ እስከ 2 ሺ ሜጋ ዋት የሚሆን ኤሌክትሪክ ወደ ውጭ ለመላክ ታስቦ የተጀመሩ ስራዎች አሉ፡፡ እዛ ውስጥ በተለያየ ሀገር ላይ ደረጃ በደረጃ ወደ ስራም ተገብቷል፡፡ መሰረተ ልማቶችን እያለማን እንገኛለን፤ እሱን እያጠናከርን መሄድ ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ሽፋን ምን ያህል ይሆናል?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር) ፡- ሕዳሴ ሲጠናቀቅ ትልቅ ትርጉም አለው፤ ኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ብዙ ስራ የሌለው ወጣት ያለባት ሀገር ነው፤ በመሆኑም ይህንን 70 በመቶ ወጣት ስራ እንዲያገኝ ካልተደረገና ኢትዮጵያን ማረጋጋት ካልተቻለ ሰው ይበዛና ስደተኛ ሆኖ ወደ ሌላ ሀገር ጋር ይሰደድና አደጋ ይከሰታል፡፡ ይህ ኢነርጅ ይህንን ኃይል ያስቀራል የሚል ዕምነት አለን፡፡ ጎረቤቶቻችንና አጋሮቻችን ጭምር ይህንን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል፤ ይሄ መሰረዊ መርሁና ጥቅሙ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ባለው የኤሌክትሪክ ሽፋንን ባለው ሕዝብ ብዛት 100 በ 100 ማድረስ የሚል ነው፡፡ የሕዳሴ ግድብ ቀድሞ ይጠናቀቃል፡፡ የሕዳሴ ግድብ ዩኒት 10 የሚያመነጨውን ሳይጨምር አሁን ያለው 4 ሺ 100 ሜጋ ዋት የሕዳሴ ግድብን ስንጨምርበት ከእጥፍ በላይ ነው የምናገኘው፡፡ እያንዳንዳቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አካባቢዎች ኃይል ያገኛሉ፤ ሰዎች ደግሞ ኃይል ባገኙ ቁጥር ስራ የመፍጠር ዕድል ይኖራል፡፡ ኢንቨስትመንት የመሳብ ስራዎች ይኖራሉ፤ እኛም በዛው ልክ እየሰራን ነው፡፡ ለዛም እንዲያመች የኢነርጅ ፖሊሲን በተለየ ሁኔታ ከልሰን እያየን ነው ያለነው፡፡ በኢነርጅ ዘርፍ በተለይ ባለሀብቱ እንዲሳተፍ፤ የግልና የመንግስት ትብብር ኢነርጅ ልማት ላይ እንዲሳተፍ ፤ መንግስት ብቻ ስለማይሆን ሕዳሴ ኃይል ካመነጨ በኋላ ስርጭቱ ላይ በግል ባለሀብቱ መታገዝ ቢችል፡፡ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ትልቅ ለውጥ እናመጣለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ኢነርጅ ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ከሕዳሴ ግድብ አንድ ተርባይን የመነጨው 375 ሜጋ ዋት ኃይል ብሔራዊ የኃይል ቋት ውስጥ ገብቷል?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር) ፡- አዎ
አል ዐይን አማርኛ፡- 375 ሜጋ ዋት ኃይል አመነጨ ሲባል፤ ምን ያህል ሰፈሮች ውስጥ ኃይል ይኖራል፤ ምን ያህል ፋብሪካዎችን ያንቀሳቅሳል?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ተከዜ 375 ሜጋ ዋት አያመነጭም፤ ወደስርዓት ገብተን ስናየው ለእኛ ትልቅ የመብራት መቆራረጥ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ከዛ ውጭ ሽፋኑን ይጨምራል፡፡ መብራት መቆራረጡን ይቀንሳል፡፡ ትርጉሙ ከዚህ በፊት መብራት ችግር ስላለ ማንቀሳቀስ ያቅት ነበር፤ አሁን እንደዛ አይሆንም፤ ማሽኖቹ ውጤታማነታቸውን ይጨምራሉ፡፡ በግለሰብ ደረጃም፤ በቤተሰብ ደረጃም መብራት መቆራረጡ ይቀንሳል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- እርስዎ የውኃና ኢነርጅ ሚኒስትር ነዎት፡፡ ቤትዎ ውስጥ መብራት ሲጠፋብዎት ምን ይላሉ? ምንስ ያደርጋሉ?
ኢ/ር ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- (ሳቅ) መብራት ሲጠፋብኝ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሻማዬን አበራለሁ፡፡