የኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ ድርሻን በሁለት ወራት ውስጥ መሸጥ እንደሚጀመር ጠ/ሚ አብይ ተናገሩ
ኢትዮጵያ ንብረት የማፍራት መብትን ለውጭ ዜጎችም ልትፈቅድ እንደምትችልም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት
ባለሀብቶች በግንባታ ዘርፍ ተወዳዳሪ ኩባንያዎችን እንዲመሰርቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለባለሀብቶች ጥሪ አቅርበዋል
ኢትዮጵያ ንብረት የማፍራት መብትን ለውጭ ዜጎችም ልትፈቅድ እንደምትችል ተገለጸ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) “ታማኝ“ ግብር ከፋዮች ከተባሉ ነጋዴዎች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡
እነዚህ “ታማኝ“ ግብር ከፋዮች የተባሉ ነጋዴዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ማብራሪያ እንዲሰጧቸው ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከልም የደህንነት ችግሮች፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት፣ የግብር እፎይታ ማነስ፣ የብድር አቅርቦት እጥረት፣ የማያሰሩ ፖሊሲዎች መብዛት እና የፖሊሲዎች በፍጥነት መቀያየር ችግሮች እንዲሁም መንግስት ለኢኮኖሚው ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸውም መንግስታቸው ባለፉት አምስት ዓመታት ኢኮኖሚውን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶችን እና በቀጣይ የመንግስታቸው ትኩረቶች ዙሪያ አድርገዋል፡፡
ከተሰጡ ምላሾች መካከልም የግብር ጉዳይ አንዱ ሲሆን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ሀብት አንድ በመቶ እንኳን ግብር እየሰበሰበች አይደለም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የ2015 ዓ.ም ዓመታዊ ምርት 10 ትሪሊዮን ብር ይደርሳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ውስጥ የተሰበሰበው ግብር 510 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው ማብራሪያ የተሰጠበት ጉዳይ የፖሊሲዎች በፍጥነት መቀያየር እና ንብረት የማፍራት መብት ጉዳይ ሲሆን ለሀገር ውስጥ ዜጎች ብቻ ተወስኖ የቆየው ንብረት የማፍራት መብት ኢኮኖሚውን የበለጠ ለማነቃቃት እና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ሲባል ለውጭ ዜጎችም ይፈቀዳል፣ ይህ ፖሊሲ በመሻሻል ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የፖሊሲ በቶሎ መቀያየር እና መሻሻል ባለሀብቶችን እና ኢኮኖሚውን ለመጥቀም ሲባል እየተደረገ መሆኑን የማያሰሩ ተጨማሪ ፖሊሲዎችም ሊሻሻሉ እንደሚችሉም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
የብድር አቅርቦትን በሚመለከት በ2015 ዓ.ም ብቻ ሁሉም ባንኮች ከሰጧቸው አጠቃላይ 540 ቢሊዮን ብር ውስጥ 85 በመቶው ለግሉ ዘርፍ እንደሆነ ነገር ግን ይህ በቂ ላይሆን እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የውጭ ምንዛሬን በሚመለከት ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ 75 ቢሊዮን ዶላር ማቅረቧን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ6 ሺህ 500 በላይ ምርት አይነቶች ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ንግዱን ለማበረታታት በሚልም መንግስት ከግብር ማግኘት የነበረበትን 85 ቢሊዮን ብር ከቀረጥ ነጻ እድል ሰጥቷልም ብለዋል፡፡
የካፒታል ገበያን በሚመለከት በሁለት ወራት ውስጥ ወደ ተግባር እንደሚገባ፣ ለዚህ የሚረዱ ፖሊሲዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርብ እለት ባጋጠመው ችግር ዙሪያ ምን አለ?
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን የኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ ድርሻን በመሸጥ ይጀመራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ወራት ውስጥ ለህዝብ መሸጥ ይጀመራል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ የአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ችግር ሲሆን አሁን ላይ አንድ ሚሊዮን የቤት እጥረት እንዳለ ችግሩን ለመፍታትም መንግስት አዋጪ እና በቀላሉ ሊታደሱ እና ሊተላለፉ የሚችሉ ቤቶች እንዲገነቡ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ባለሀብቶች በግል እየመጣችሁ መሬት አትጠይቁን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደራጀ እና ኩባንያ እንዲመሰርቱ፣ በሪል እስቴት፣ ብረት ማምረት እና ሌሎች የግንባታ ቁሳቁስ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ወደ ማምረት እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተሸለ ህክምና ፍለጋ በሚል በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደምታጣ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለሀብቶች ይህንን ሀብት ለማስቀረት በህክምና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩም ምክረ ሀሳባቸውን አቅርበዋል፡፡