በሩሲያ ሞስኮ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 115 ደርሷል
ኢትዮጵያ በሩሲያ ሞስኮ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት እንደምታወግዝ ገለጸች።
በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በሚገኘው ኮርኩስ ሲቲ ሆል አዳራሽ ውስጥ እየተካሄደ በነበረ የሙዚቃ ድግስ (ኮንሰርት) ላይ ታጣቂዎች ትናንት ምሽት ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
ታጣቂዎቹ በአውቶማቲክ የጦር መሳሪያ እና በቦምብ ባደረሱት ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ115 የተሸገረ ሲሆን፤ የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ145 ማለፉ ነው የተነገረው።
ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ፤ በሞስኮ የተፈጸመውን ጭካኔ የተሞላበት የሽበር ጥቃት እንደምታወግዝ አስታውቃለች
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው “ኢትዮጵያ አርብ መጋቢት 13 ምሽት ላይ በሞስኮ በሚገኘው ክሮከስ ሲቲ ሆል የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በንፁሀን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አረመኔያዊ እና አሰቃቂ የሽብር ጥቃት ታወግዛለች” ብሏል።
በሽብር ጥቃቱ ሰለባ በሆኑት ንፁሃን ዜጎች የተሰማውን ልባዊ ሀዘን በመግለጽ ለሩሲያ መንግስት እና ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቷል።
“ሽብርተኝነት በሰው ልጅ ላይ የተደቀነ ትልቅ አደጋ ነው” ያለው የኢትዮጵያ መንግስት መግለጫ፤ “እንዲህ አይነቱን የንጹሃን የህይወት መጥፋት ለመከላከል የዓለም ሀገራት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል” ብሏል።
“ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሩሲያ ፌዴሬሽን መንግሥትና ከሩሲያ ህዝብ ጎን ትቆማለች” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር በመግለጫው አረጋግጧል።
ሩሲያ አሸባሪዎችን ለመዋጋት ለምታደርገው ጥረት የኢትዮጵያ ሙሉ ድጋፍ እንደምትሰጥም መግለጫው አስታውቋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማፊያ ዛራኮቫ ትና የትናንት ምሽቱን ጥቃት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፣ ይህንን አረመኔያዊ ተግባር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዘው ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም በርካታ ሀገራት ለሩሲያ አጋርነታቸውን በማሳየት መግለጫ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በሽበርተኘት የተፈረጀው ኢስላሚክ ስቴት (አይ.ኤስ) ለጥቃቱ ኃላፊነት እንደሚወስድ ያስታወቀ ሲሆን፤ የአይ ኤስ ክንፍ የሆነው የአፍጋኒስታኑ የኮርሳን ፕሮቪንስ ኢስላሚክ ስቴት ጥቃቱን ያደረሱት አባላቱ እንደሆኑ ገልጿል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቤተ መንግስት ክሬምሊን በጥቃቱ ዙሪያ እስካሁን ተጠያቂ ያደረገው አካል የለም የተባለ ሲሆን፤ ሆኖም ግን የተወሰኑ የሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዩክሬንን ተጠያቂ ለማድረግ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ መይክሃይሎ ፖዶልያክ፤ ዩክሬን በዚህ ተግባር ውስጥ እጇ የለበትም ሲሉ አስተባብለዋል።
“ዩክሬን የሽብር መንገድን ተጠቅማ አታውቅም” ያሉት አማካሪው፤ “በጦርነቱ ውስጥ ያሉ ጉዳዮች ሁሉ መፍትሄ የሚያገኙት በጦር ግንባር ነው” ብለዋል።