8 የአውሮፓ ሀገራት ያገዱትን የአስትራዜኔካ ክትባት ኢትዮጵያ መስጠት እንደምትቀጥል ገለጸች
ኢትዮጵያ አስትራዜኔካ የተሰኘውን ክትባት ትናንት መስጠት ጀምራለች
የደም መርጋት ችግር ያስከትላል በማለት እስካሁን 8 የአውሮፓ ሀገራት የአስትራዜኔካ ክትባት መስጠት አቁመዋል
እስካሁን 8 የአውሮፓ ሀገራት ያቆሙትን አስትራዜኔካ የተሰኘውን የኮሮና ቫይረስ ክትባት ኢትዮጵያ ክትባቱን መስጠት እንደምትቀጥል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በጤና ሚኒስቴር የህክምና አግልጋሎት ዋና ኃላፊ አቶ ያዕቆብ ሰማን ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት በርካታ ሀገራት ክትባቱን እንዳቆሙ ብንሰማም ክትባቱ በትክክል የተባለውን ችግር እንደሚያስከትል በጥናት የተረጋገጠ ነገር የለም ብለዋል።
በመሆኑም አስትሬዜኔካ ክትባት የደም መርጋት ችግር እንደሚያደርስ በሳይንስ የተረጋገጠ ነገር እስከሌለ ድረስ ኢትዮጵያም ክትባቱን ለዜጎቿ መስጠቷን ትቀጥላለች ሲሉ አቶ ያዕቆብ ተናግረዋል።
እስካሁን 8 የአውሮፓ ሀገራት የአስትራዜኔካ ክትባት የደም መርጋት ችግር ያስከትላል በሚል ምክንያት ክትባቱ ለዜጎቻቸው እንዳይሰጥ ከልክለዋል፡፡
አየርላንድ፣ ዴንማርክ፣ኦሰትሪያ፣ቡልጋሪያ፣ አየስላንድ፣ ጣልያን እና ኖርዌይ ክትባቱ ለዜጎቻቸው እንዳይሰጥ ያገዱ ሀገራት ናቸው።
ክትባቱ በኢትዮጵያ በትናንትናው እለት በፌደራል ደረጃ በአዲስ አበባና በክልሎች መሰጠት ተጀምሯል፡፡
ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዙር 2.2 ሚሊዮን የአስትራዜነካ ክትባት በህንዱ ሴረም ኢኒስትቲዩት የተመረተ ክትባት ባለፈው ሳምንት መረከቧ ይታወሳል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጨመሩንና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የኮሮና ጽኑ ህሙማን ቁጥርም አሻቅቧል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በኢትዮጵያም የኮቪድ 19 ቫይረስ የመሰራጨት አቅሙን ጨምሮ አስጊ በሆነ ደረጃ በ12.80 በመቶ መድረሱን ገልጾ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እስከ መጭው ታህሳስ 2014ዓ.ም ድረስ 20 በመቶ የሚሆነውን ህዝቧን ለመከተብ ማቀዷን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡