ከ20 ወራት በላይ ደመወዝ ያላገኙት የትግራይ ክልል የመንግስት ሰራተኞች ቀጣይ ተስፋ ምንድን ነው?
ጄነራል ታደሰ ወረደ፤ “የመንግስት ሰራተኛው እስካሁን ጠብቆናል፤ ተጨማሪ ጊዜ መጠበቅ የለበትም” ብለዋል
የደመወዝ መዘግየት “የመንግስት ሰራተኛው በክልሉ አመራር ላይ የነበረውን እምነት እንዲቀንስ ያደረገ ነው” ተብሏል
ለሁለት አመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት 220ሺህ በሚሆነው የትግራይ ክልል የመንግስት ሰራተኞች ላይ ያስከተለው የኢኮኖሚ ችግር ከፍተኛ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጽ የቆየ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አል-ዐይን አማርኛ በስልክ ያናገራቸው አቶ ክብሮም፣አቶ መሓሪ እና ወ/ሮ ህይወት የተባሉ የትግራይ ክልል የመንግስት ሰራተኞች የሚናገሩትም ጦርነቱ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ኑሮ ሲመራ በነበረው “ሲቪል ሰርቫንት” ላይ ከፍተኛ ቀውስ ማስከተሉ ነው፡፡
ከሰኔ 2013 በኋላ ከ20 በላይ ለሚሆኑ ወራት እንደማንኛውም የክልሉ የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ አለማግኘታቸውን የተናገሩት የመንግስት ሰራተኞቹ፤ “በህይወታችን ከባድ የሚባለውን ጊዜ እና ፈተና እያሳለፍን ነው” ብለዋል፡፡
የመንግስት ሰራተኞቹ የመቶ ሺዎች ህይወት የቀጠፈውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማቆም በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙ ቢያንስ የጥይት ድምጽ ባለመስማታቸው ቢደሰቱም ያለ ደመወዝ መኖር አሁንም ህይወታቸውን ከባድ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡
የፌደራል መንግስት፤ የትግራይ ክልል የመንግስት ሰራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን በጀት እንዲለቀቅ ከተፈለገ መጀመሪያ ጊዜያዊ መንግስት ሊቋቋም ይገባል የሚል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡ የትግራይ ተደራዳሪ ቡድን መሪና የህወሓት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
አቶ ጌታቸው ፌዴራል መንግስት ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ ባናምንበትም ለህዝባችን ስንል ጊዜያው መንግስትን በአጠረ ጊዜ እናቋቁማለን ሲሉም ነበር የተናገሩት በወቅት፡፡
ይሁን እንጅ በፕሬቶሪያው ስምምነት መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቋቋማል የተባለው ጊዜያዊ መንግስት ሳይቋቋም ከሶስት ወራት በላይ ሆኖት፤ የትግራይ የመንግስት ሰራተኞች ስቃይ እንደቀጠለ ነው፡፡
“የመንግስት ሰራተኛው በአመራሩ የነበረውን እምነት ቀንሷል”
የመንግስት ሰራተኞቹ እንደሚናገሩት ከሆነ የሰላም ስምምነቱ አተገባበር በተለይም የጊዜያዊ መንግስት የማቋቋሙ ሂደት መዘግየት በሲቪል ሰርቫንት ላይ ቅሬታ እየፈጠረ መምጣቱ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱም አከላት ከስምምነት ሲደርሱ ነገሮች ተስተካክለው ደመወዝ አገኛለሁ የሚል ተስፋ አድሮብኝ ነበር የሚሉት አቶ ክብሮም ፤ አሁን የማስተውላቸው አካሄዶች “እውነት እንዚህ ሰዎች ስለ ህዝብ ይጨነቃሉ ?” የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አድርጎኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሁኔታው “የመንግስት ሰራተኛው በክልሉ አመራር ላይ የነበረውን እምነት እንዲቀንስ ያደረገ ነው” ሲሉም አክለዋል ላለፉት 20 አመታት ያህል በተለያዩ የክልሉ መስሪያ ቤቶች ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ክብሮም፡፡
ከስምምነቱ በኋላ የመንግስት ሰራተኛው ደመወዝ ያገኛል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው የሚናገሩት ሌላኛው የክልሉ የመንግስት ሰራተኛ አቶ መሓሪም እንዲሁ፤ መዘግየቱ ለሁለት አመታት ገደማ ደመወዝ ሳያገኝ ለቆየው ሲቪል ሰርቫንት ከባድ መሆኑን ግልጸዋል፡፡
“እንደዚህ የሚዘገይ ከሆነ የፌደራል እና የክልሉ መንግስታት ቢያንስ የተለየ አሰራር በመዘርጋት ሲቪል ሰርቫንቱ የተወሰነ ድጋፍ የሚያገኝበት አማራጭ ማበጀት ነበረባቸው” ብለዋል፡፡
የመንግስት ሰራተኛው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ደመወዝ ጠብቆ ነበረ ቢሆንም የሚስተዋለው መዘግየት በክልሉ ሲቪል ሰርቫንት ላይ ቅሬታ መፍጠሩ እንዳልቀረ የገለጹት ደግሞ ላላፉት 15 አመታት በመንግስት ሰራተኝነት ያገለገሉት ወ/ሮ ህይወት ናቸው፡፡
“ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የተራበው የመንግስት ሰራተኛው እንጅ ስልጣን አልነበረም” ሲሉም ያለውን ችግር ክብደት ገልጸውታል፡፡
የፌዴራል እና የክልሉ መንግስታት ለተገቸረው ህዝብና የመንግስት ሰራተኛ ሲባል አሁንም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲሉም ጠይቋል ወ/ሮ ህይወት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ክልል የመንግስት ሰራተኞችና ጡረተኞች ያሉበት ሁኔታ እጅግ ከባድ መሆኑ ዘጠኝ አባላት ያሉት የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ከቀናት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
“የመንግስት ሰራተኛው እስካሁን ጠብቆናል፤ ተጨማሪ ጊዜ መጠበቅ የለበትም፤ እስካሁንም መዘግየት ያልነበረበት ጉዳይ ነው” ሲሉም ነበር የተናገሩት የኮሚቴው ሊቀ መንበር ጄነራል ታደሰ መንግስት የሚመሰረትበት ሰነድ መዘጋጀቱን በገለጹበት ወቅት፡፡
ጄነራሉ የትግራይ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ጉዳይ መፍትሄ የሚሰጠውና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግስት የሚመሰረትበት ሰነድ በቀጣይ ሳምንት ይፋ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡
ጄነራሉ ይፋ ስለሚደረገው ሰነድ እንጅ ጊዚያዊ መንግስት ተቋቁሞ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ የሚያገኙበት ጊዜ መች እንደሆነ ግን አላመላከቱም፡፡
የሚቋቋመው ጊዚያዊ መንግስት ዋና ተልዕኮ የትግራይን ህዝብ ጥቅም ማስጠበቅ እንደሆም ተናግረዋል ጄነራሉ፡፡