ኢትዮጵያና አረብ ኤምሬትስ በ17 መስኮች በጋራ ለመስራት ተስማሙ
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር መክረዋል
ኤምሬትስ በኢትዮጵያ የምታደርገው ኢንቨስትመንት 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ደርሷል
ኢትዮጵያ እና አረብ ኤምሬትስ በ17 መስኮች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል።
ከፕሬዝዳንቱ ጋር አዲስ አበባ የገባው የኤምሬትስ ልኡክም በውይይቱ ላይ ተሳትፏል።
በዚህ የሁለትዮሽ ምክክር የኢትዮጵያ እና አረብ ኤሚሬትስ ሁለንተናዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሄዱ ተመላክቷል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በተለይም ለሁለቱ ህዝቦች እና ለመጪው ትውልድ ግንኙነት ጠንካራ ድልድዮችን ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነትም በዚሁ ወቅት አረጋግጠዋል።
የኤምሬትስ ልኡክ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ካደረገ በኋላም በ17 ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችሉ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራርመዋል።
ሀገራቱ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት እና በፋይናንስ ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት ነው የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙት።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2004 በኤምሬትስ ቆንስላ ጽህፈት ቤቷን ስትከፍት በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ እና አረብ ኤምሬትስ ግንኙነት ባለፉት ሁለት አስርት እየጎለበተ ሄዷል።
በ2010 በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን የከፈተችው አቡ ዳቢ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አጠናክራለች።
ኤምሬትስ ለኢትዮጵያ ያደረገችው ድጋፍ 5 ቢሊየን ዶላር ተሻግሯል፤ በኢትዮጵያ የምታደርገው ኢንቨስትመንትም 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
የሀገራቱ የንግድ ልውውጥም በ2022 ብቻ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉ አለማቀፍ የኤምሬትስ ኩባንያዎች ቁጥርም እያደገ የሄደ ሲሆን፥ ዛሬ በአዲስ አበባ የተፈረሙት 17 የመግባቢያ ስምምነቶችም የኤምሬትስን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንደሚያሳድጉ ይጠበቃል።