ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን በያዙ በሶስተኛ ወራቸው ኤምሬትስን መጎብኘታቸው ይታወሳል
ከ100 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በሰላም የሚኖሩባት ኤምሬትስ ባለፉት አምስት አመታት ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መስርታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጡም በቅድሚያ ከጎበኟቸው ሀገራት መካከል አረብ ኤምሬትስ ቀዳሚዋ ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ሚኒስትሮችን ያካተተ ልኡካቸውን እየመሩ በግንቦት 2018 በአቡ ዳቢ የሶስት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በዚያው አመት ከሶስት ወራት በኋላም ወደ ኤምሬትስ አቅንተዋል፤ የ”ዛይድ ሽልማት”ን ለመቀበል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የ20 አመት ሰላምም ጦርነትም የሌለው ውጥረት ፈተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስመራ፤ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም አዲስ አበባ እንዲገኙና የሰላም አየር እንዲነፍስ ኤምሬትስ ትልቁን ድርሻ ትወስዳለች።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ውጥረት ረግቦ ሰላም እንዲነግስ ላደረጉት ጥረትም አቡ ዳቢ የ”ዛይድ ሽልማት” ማበርከቷ አይዘነጋም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ እና ኤምሬትስ የሁለትዮሽና ቀጠናዊ ትብብር ይጎለብት ዘንድ በተደጋጋሚ ወደ አቡ ዳቢ በማቅናት ምክክር አድርገዋል።
ኤምሬትስም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን በመጋቢት 2018 ወደ አዲስ አበባ በመላክ ከኢትዮጵያ ጋር በበርካታ ዘርፎች የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች።
ሰኔ 15 2018 ላይ የወቅቱ የአቡ ዳቢ ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ዛይድ አዲስ አበባ መግባታቸውም የሀገራቱን ትብብር የማሳደግ ፍላጎት ማሳያ ነው።
በአዲስ አበባ የሁለትዮሽ ትብብርን የሚያሳድጉ ስምምነቶችን ተፈራርመው ወደ ሀገራቸው የተመለሱትና የአሁኑ የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ናቸው።