ሞሃመድ ቢን ዛይድ - የመካከለኛው ምስራቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሪ
የአሜሪካው ወልስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ባወጣው ሀተታ፥ አረብ ኤምሬትስ በሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ መሪነት የአለም ጂኦፖለቲካን እየቀየረች እንደምትገኝ ገልጿል
ከአሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይና ጋር የመሰረቱት ጠንካራ ግንኙነትም የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሲጀመር እንኳን አልተፈተነም ብሏል ጋዜጣው
ሰላምና መረጋጋት በራቀው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና አንድ ብርቱና ተደማጭ መሪ ከሀገራቸውና ቀጠናው አልፈው አለምአቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ እየሆኑ ይገኛሉ ይላል የአሜሪካው ጋዜጣ ወልስትሪት።
ትብብር እና ንግግር ላይ ያተኮረ ዲፕሎማሲን የሚከተሉ፤ በፈተና የሚጸኑና ወንድማማችነትን በተግባር የሚያሳዩ መሪ፤ የአረብ ኤምሬትሱ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን።
“አረብ ኢሚሬትስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስተማማኝ የኃይል አቅራቢ ሆና ትቀጥላለች”- ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ
ጋዜጣው ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድን “የመካከለኛው ምስራቅ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሪ” ሲል ገልጿቸዋል።
ወልስትሪት ጆርናል አረብ ኤምሬትስ በሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ መሪነት የአለም ጂኦፖለቲካን እየቀየረች እንደምትገኝ ነው በሀተታው ያሰፈረው።
በተለይ ሩሲያ እና ዩክሬን በየካቲት ወር 2022 ጦርነት ውስጥ ከገቡ በኋላ የከወኗቸው ተግባራት ኤምሬትስን በአለም ጂኦፖለቲካ አሸናፊ ያደረጋት እንደነበር ያትታል።
ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ የጦርነቱን አውድ አስቀድሞ በመረዳትና የወደፊቱን በመተንተን የጋራ ትብብር እና መከባበርን መሰረት ያደረጉ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በመስራታቸውም የተገኙ ውጤቶችን ዘርዝሯል ጋዜጣው።
በዩክሬን ጦርነት ገለልተኛ አቋም የያዘችው ኤምሬትስ ከአሜሪካም ሆነ ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ጠንካራ ግንኙነትን መስርታለች።
ሀገሪቱ ባለፈው አመት በተቀሰቀሰው ጦርነት ወደአንዱ ጎራ ከመሰለፍና በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ከጦርነቱ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ከኬቭ ጋርም ወዳጅነቷን ማስቀጠሏ ታማኝነትን ፈጥሮላታል ነው የሚለው የወልስትሪት ጆርናል ዘገባ።
ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ከሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ ሞሃመድ ቢን ሳልማን ጋር በመሆን አሜሪካ እና ሩሲያ እስረኞች እንዲለዋወጡ አድርገዋል።
ይህም በዋሽንግተን እና ሞስኮ ባለስልጣናት መወደሱን ያነሳው ዘገባው፥ የዩክሬኑን ጦርነት ተከትሎ አለም የተለያዩ ፈተናዎችን ስታስተናግድና ሃያላኑ ሀገራት ፉክክር ውስጥ ሲገቡ አቋሟን አለወጠችም ብሏል።
ከአሜሪካ ጋር ያላት ወዳጅነት ከሩሲያ እና ቻይና ጋር የመሰረተችውን ትብብር በምንም መልኩ እንዲረብሸው አለመፍቀዷን የሚያሳዩ ውሳኔዎችንም ማሳለፏን ነው ወልስትሪት ጆርናል ያስነበበው።
የነዳጅ ዋጋን ለማረጋጋት የነዳጅ አምራችና ላኪ ሃገራት (ኦፔክ) ምርታቸውን እንዲቀንሱ ኤምሬትስ የመሪነት ድርሻ እንደነበራትም በመጥቀስ።
ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የሃያላኑ ሀገራት ፉክክር በኤምሬትስ ፖሊሲዎች እና ፍላጎቶች ላይ ጫና እንዲያሳድሩ በር አለመክፈታቸውም በመካከለኛው ምስራቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሪ ሆነው እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል ነው ያለው ዘገባው።
ሽብርተኝነት መዋጋትና የኢነርጂ ገበያን ማረጋጋት
ይኸው ጋዜጣ እንደገለጸው አሜሪካ አረብ ኢምሬትስን ሽብርተኝነትን በመዋጋትና የኢነርጂ ገበያን በማረጋጋት ዋነኛ አጋሯ አድርጋታለች።
ጋዜጣው የሆዚ ታጣቂዎች በፈረንጆቹ 2022 አቡዳቢን ያጠቁ ጊዜ አለም ሁሉ አጋርነቱን ሲገልጹ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለሼህ መሀመዶ ቢን ዛይድ ደውለው አጋርነት አለማሳየታቸውን በድክመት ጠቅሷል።
ጋዜጣው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገን የአሜሪካ ባለስልጣን ጠቅሶ ሼህ መሃመድ ቢን ዛይድ የአሜሪካ አቋም ምን እንደሆነ ማብራሪያ ጠይቀው ነበር ብሏል።
ይህን ተከትሎም አሜሪካ ሼህ መሃመድ ቢን ዛይድን ወደ ዋሽንግተን መጋበዟን እና አሜሪካም ከአረብ ኢምሬትስ ጋር በኢነርጂ፣በንግድ እና በደህንነት ለመስራት ቃል መግባቷ ይታወሳል።
እኝህ ባለስለጣን እንደተናገሩት ሼህ መሃመድ ቢን ዛይድ በፈረንጆቹ 2022 በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ አጋር ከሆነችው እስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን አድሰዋል።
በዚህም አረብ ኢምሬት ከተመሰረተች ጀምሮ አሜሪካ ወሳኝ አጋሯ መሆኖንም ገልጸዋል።