ኢትዮጵያ 10ኛውን የሚዳሰስ ቅርስ በዩኔስኮ አስመዘገበች
የጌድኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ 10ኛው ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ብዙ ቅርሶች ያላቸው ሀገራት ደረጃን ከደቡብ አፍሪካ ጋር ትመራለች
ኢትዮጵያ 10ኛውን የሚዳሰስ ቅርስ በዩኔስኮ አስመዘገበች።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅትወይም ዩኔስኮ 45ኛ ጉባኤውን በሳውዲ አረቢያ ሪያድ እያካሄደ ይገኛል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ጌዴኦ ዞን የሚገኘው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ተገልጻል።
ዩኔስኮ በድረገጹ እንዳስታወቀው የጌድኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር 10ኛው ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን ለዓለም አብስሯል።
ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 10 ቅርሶችን በዩኔስኮ መዝገብ ስር በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበች ሲሆን ከደቡብ አፍሪካ ጋር በአንደኝነት ይመራሉ።
ሞሮኮ በአፍሪካ ከኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ዘጠኝ ቅርሶችን በዩኔስኮ ስታስመዘግብ ቱኒዝያ ስምንት እንዲሁም ግብጽ፣ ሴኔጋል እና ታንዛኒያ ደግሞ ሰባት ቅርሶችን ያስመዘገቡ ሀገራት ናቸው።
ኢትዮጵያ በሪያድ እየተካሄደ ባለው የዩኔስኮ ጉባኤ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት ዳይሬክተር አበባው አያሌው እና ሌሎች ባለሙያዎች ተወክላለች።
ዛሬ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጌድኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር በዕጽዋዕት፣ ፍራፍሬ እና በሰብል ምርቶች ታዋቂነትን ያተረፈ እንደሆነ ተገልጿል።
እንዲሁም መልክዓ ምድሩ ህብረተሰቡ ሀገር በቀል ዕውቀት ተጠቅሞ የአየር ሚዛን የተስተካከለ እንዲሆን በማስቻል እንዲሁም የመሬት አጠባበቅ እና አያያዝ ልምዱ ለሌሎች ህዝቦች ልዩ ተሞክሮና ልምድ የሚሰጥ ነውም ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የዚህ መልክዓ ምድር አንድ አካል የሆነው ይህ የዓለም ቅርስ በውስጡ የትክል ድንጋይ መካነ ቅርስንም ይዟል።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጌድኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በውስጡ ከ6 ሺህ በላይ ትክል ድንጋዮችን የያዘ ሲሆን ተጨማሪ ጎብኚዎችን ለኢትዮጵያ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ይህን ቅርስ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ላለፉት 10 ዓመት በይፋ አመልክታ ክትትል ስታደርግ እንደነበር ተገልጿል።