በባህላዊ መንገድ የሚጋገረው “ባጌት” በብዙሃኑ ፈረንሳዊያን ዘንድ እንደሚዘወተር ይነገራል
ፈረንሳይ “ባጌት” ተብሎ የሚጠራው ታዋቂው ባህላዊ ዳቦ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብላት የዓለም የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ)ንጠየቀች፡፡
ፈረንሳውያን በዓመት 10 ቢሊዮን ገደማ “ባጌት” እንደሚመገቡ ‘ፕላንቶስኮፕ’ የተባለው የመረጃ ገጽ ጠቁሟል።
ሆኖም አሁን አሁን ግን ብዙሃኑ ፈረንሳያውያን ከአነስተኛ ዳቦ ቤቶች “ባጌት” መግዛት አቁመው ወደ ትልልቅ መደብሮች መዛወራቸው ይነገራል፡፡
በዚህም ምክንያት እኤአ ከ1970 ወዲህ 20 ሺ የሚደርሱ አነስተኛ ዳቦ ቤቶች መዘጋታቸው ነው የሚነገረው፤ ምንም እንኳ እነዚህ ትልልቆቹ መደብሮች ባህላዊውን መንገድ ተከትለው ዳቦውን ባይጋግሩም፡፡
“ባጌት” ቅርስ ሆኖ ከተመዘገበ ዳቦው የሚዘጋጅበት ባህላዊ ሂደት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር የአዘገጃጀት እውቅቱም የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
በመዝባሪዎች እንዳይሰረቅ ጥበቃ እንደሚደረግለትም ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
ዩኔስኮ ከአሁን ቀደም የኢራን እና የካዛኪስታን ባህላዊ ዳቦዎችን በዓለም ቅርስነት መዝግቧል።
ፈረንሳይ በቅርስነት ልታስመዘግብ አስባ ከነበረው መካከል በዚንክ የሚሠራ የቤት ጣሪያ እና “ቢዮ አርቦይስ” የተባለ የወይን ፌስቲቫል ይጠቀሳሉ።
ሆኖም “ባጌት” ቀዳሚ ሆኖ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ከወደ ፓሪስ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
ዩኔስኮ በቀጣዩ ዓመት ለጥያቄው ይፋዊ ምላሽ እንደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ቀደም የደቡብ ኮርያ የፋኖስ ፌስቲቫል፣ የፊንላንድ የሳውና ባህል፣ የቦሲኒያ እና ሄርዞጎቪኒያ የሳር አጨዳ ውድድር በቅርስነት ተመዝግበዋል።