ሊቨርፑል ከቅርስነት መዝገብ የተሰረዘችው የዩኔስኮ አመራሮች በሰጡት ሚስጥራዊ ድምጽ ነው
የተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ ሊቨርፑልን ቅርስ ከሆኑ የዓለም ከተሞች ዝርዝር መሰረዙን አስታወቀ፡፡
ዩኔስኮ ከተማይቱን ከዝርዝሩ የሰረዘው የኤቨርተን እግር ኳስ ቡድን ስቴዲዬም (ጉዲሰን ፓርክ)ን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የልማት ፕሮጄክቶች የከተማዋን ታሪካዊ የውሃ ዳርቻ (The Liverpool Waterfront) “ትክክለኛነት እና ታማኝነት” የዓለም ቅርስነት አደጋ ላይ በመጣላቸው ነው፡፡
በዚህም ዩኔስኮ የድርጅቱ አመራሮች በሰጡት ሚስጥራዊ ድምጽ ሊቨርፑልን ከቅርስነት መዝገብ መሰረዙን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
በቻይና በተሰናዳው የዩኔስኮ ኮሚቴ ስብሰባ ጓቲማላን፣ማሊን እና ክርዚጊስታን ጨምሮ 21 ሀገራት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በዚህም 13 ሀገራት ሊቨርፑል ከቅርስነት እንድትሰረዝ ድምጽ ሲሰጡ 5 ተቃውመዋል፡፡ የተቀሩት ሁለት ድምጾች ዋጋ አልባ ሆነው ሳይቆጠሩ ሲቀሩ አንድ ሀገር ሳትሳተፍ ቀርታለች፡፡
በዚህም ውሳኔን ለማሳለፍ የሚያስፈልገው 2/3ኛ ድምጽ ብቻ በመሆኑ ሊቨርፑል ከቅርስነት መዝገብ እንድትሰረዝ ሆኗል፡፡
የስበሰባው ሊቀ መንበር ትያን ዡጁን “ረቂቅ ውሳኔው ፀድቋል፤ ይህ ማለት የሊቨርፑል የባህር ላይ ንግድ ቦታ ከዝርዝሩ ተሰርዘዋል ማለት ነው” ብለዋል፡፡
ወደዚህ ውሳኔ የተደረሰው የእንግሊዝ መንግስት ቅርሶቹን ከመጠበቅ አንጻር ግዴታዎቹ ስላልተወጣ መሆኑንም ነው የዩኔስኮ ኮሚቴ አመራሮች የገለጹት፡፡
ሆኖም ውሳኔው የከተማይቱን ባለስልጣናት አስቆጥቷል፡፡ ውሳኔው ሊገባ የማይችል ነው ያሉት የከተማዋ ከንቲባ ጆአን አንደርሰን ዩኔስኮ ዳግም ታድሰው ለመዘመን የሚፈልጉ ከተሞችን እየቀጣ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ጥንታዊቷ የወደብ ንግድ ከተማዋ ሊቨርፑል እ.ኤ.አ በ2004 ነበር፤ ልክ እንደ ጣሊያኗ ቬኒስ፣ እንደ ህንዱ ታጅ መሐል፣እንደ ግብጽ ፒራሚዶች ሁሉ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበችው፡፡
ሆኖም ከ2012 በኋላ ልክ በኢራቅ፣ በሶሪያ እና ፍልስጤም እንደሚገኙ ቅርሶች ሁሉ አደጋ ላይ ትገኛለች በሚል በዩኔስኮ 'የአደጋ ዝርዝር' ውስጥ ሰፍራለች፡፡
ይህ የሆነው በባህር ዳርቻው ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘውን የከተማይቱን ወደብ መልሶ ለመገንባት የቀረበው የ5 ቢሊዬን ፓውንድ እቅድ በ2013 በመጽደቁ ነው፡፡