የሬሚዳል ፕሮግራምን ለመከታተል የመመዝገቢያ ነጥብ በመንግስት እና በግል ዩኒቨርሲቲዎች ይለያያል?
የግል ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን በአንደኛ ዓመት እና በሬሚዳል ፕሮግራም ወጥ ባልሆነ መንገድ በመመዝገብ ላይ ናቸው
የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ይፋ ሆኖ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸውን እየተቀበሉ ነው
በኮሮና ቫይረስ እና ሌሎች ተጽዕኖዎች ምክንያት ዘግይቶ የተሰጠው የ2014 ዓ. ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ውጤት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ጥቂት ተማሪዎች እንዳለፉበት የተገለጸው ይህ የፈተና ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን. በተለያዩ ፕሮግራሞች በመቀበል ላይ ይገኛሉ።
አል ዓይን አማርኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገውን የመመዝገቢያ ውጤት ዩኒቨርሲቲዎች ምን ያህል እየተገበሩ ነው? ሲል ምልከታ አድርጓል።
በአዲስ አበባ በአካል እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጪ በስልክ ባደረግነው ማጣራት በተለይም የግል ዩኒቨርስቲዎች እና ኮሌጆች ትምህርት ሚንስቴር ባስቀመጠው ፕሮግራም እና የመመዝገቢያ ነጥብ መሰረት ተማሪዎችን እየመዘገቡ መሆኑን ታዝበናል።
ይሁንና በትምህርት ሚኒስቴር ከተቀመጠው የአቅም ማሻሻያ ወይም ሬሚዳል ስልጠና ፕሮግራም መመዝገቢያ ነጥብ በታች ያመጡ ተማሪዎችን እየመዘገቡ ያሉ ዩኒቨርስቲዎች እና ኮሌጆች መኖራቸውን ተመልክተናል።
ትምህርት ሚኒስቴር በተለይም ከ50 በመቶ በታች ያመጡ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የሬሚዳል ፕሮግራምን በተለያዩ አማራጮች እንዲከታተሉ የመቁረጫ ነጥብ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።
የመቁረጫ ነጥቡ ለታዳጊ እና አርብቶ አደር ባልሆኑ ክልሎች የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ለወንድ 263 ከ700 ለሴት ደግሞ 227 ሲሆን ለማህበራዊ ሳይንስ ለወንድ 220 ከ600 እንዲሁም ለሴት 190 ከ600 መሆኑን ማሳወቁም የሚታወስ ነው።
በዚህ የሬሚዳል መቁረጫ ነጥብ መሰረት ባደረግነው ምልከታ ከተቀመጠው ነጥብ በታች ያመጡ ተማሪዎችን የሚመዘግቡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መሆራቸውን አይተናል።
ምዝገባውን እያከናወነ ላለው ዩኒቨርሲቲ እና ኮሎጁ ትምህርት ሚኒስቴር ካስቀመጠው ነጥብ በታች ያመጡ ተማሪዎችን ለምን መዘገባችሁ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ መንግሥት ይፋ ያደረገው ለመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች እንጂ ለግል ተቋማት አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።
አል ዓይን ይህን ጥያቄ ይዞ ትምህርት ሚኒስቴርን የጠየቀ ሲሆን የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙንኬሽን ሀላፊ ወይዘሮ አመለወርቅ እዝቅኤል፥ "ለሬሚዳል ፕሮግራምም ይሁን ከ50 በመቶ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች መመዝገቢያ ነጥብ ለመንግሥትም ይሁን ለግል ዩኒቨርሲቲ ተመሳሳይ ነው" ሲሉ ተናግረዋል ።
ከዚህ በፊት የነበረው ለግል እና ለመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች የተማሪዎች መመዝገቢያ ነጥብ ይለያይ ነበር ያሉት ሀላፊዋ፥ ከ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በኋላ ተመሳሳይ እንዲሆን መወሰኑን አክለዋል።
በዚህም መሰረት ትምህርት ሚኒስቴር ካስቀመጠው የሬሚዳል ፕሮግራም መመዝገቢያ ነጥብ ውጪ የሚመዘግቡ ዩኒቨርስቲዎች እና ኮሌጆች ህግ እየጣሱ መሆኑንና እርምጃም እንደሚወሰድባቸው ነው ያብራሩት።