በጦርነት ምክንያት ከሶስት ጊዜ በላይ ተፈናቅላ ከፍተኛ ውጤት ያመጣችው የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ
ቤተሰቦቼ እና መምህራን የጦርነቱን ጠባሳ እንድረሳ አግዘውኛል- ተማሪ ገሊላ
ሳይንቲስት የመሆን ህልም ያላት ተማሪ ገሊላ ውጤቴ ባልረካም ወደ ዩንቨርሲቲ የሚያስገባኝ ስለሆነ አይከፋኝም
በጦርነት እና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ዘግይቶ የተሰጠው የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ከሰሞኑ ይፋ ተደርጓል።
900 ሺህ ገደማ ተማሪዎችን ያስፈተነችው ኢትዮጵያ ፈተናውን ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር ግን 30 ሺህ እንኳን አልሞላም። ይህ ሁሉ ተማሪ ስለምን ከ50 በመቶ በታች ሊያመጣ ቻለ? ለሚለው ጥያቄ ብዙዎች የየራሳቸውን መላ ምት ቢያስቀምጡም ጉዳዩ ግን ጥናት የሚያስፈልገው ይመስላል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በየቦታው የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች በተማሪዎች ስነ ልቦና ላይ የራሳቸውን ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም። በአማራ ክልል የሚገኙት አጣዬ እና ሸዋሮቢት ከተሞች አውዳሚ የተባሉ ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግሮችን ካስተናገዱ አካባቢዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
አል ዐይን አማርኛ በነዚህ አካባቢዎች ስለነበሩ የ12ኛ ክፍል ፈተና እና ውጤቶችን ለመዳሰስ ሞክሯል። ተማሪ ገሊላ አሰፋ ትባላለች፤ ከህጻንነቷ ጀምሮ ሳይንቲስት የመሆን ህልምን ይዛ ትምህርቷን ስትከታተል የነበረችው ገሊላ በአጣዬ ከተማ ተወልዳ ማደጓን ነግራናለች።
“የደረጃ ተማሪ መሆኔ ምኞቴ እንደሚሳካ የእርግጠኝነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርገኛል” የምትለው ተማሪ ገሊላ “በአካባቢያችን በተደጋጋሚ የተከሰቱት ጦርነቶች አስጨናቂ እና ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ” ብላለች።
“በተለይ ደግሞ 11ኛ ክፍል ተማሪ እያለች በ2013 ዓ.ም ላይ የተከሰቱት ሁለት ግጭቶች መኖሪያ ቤታችንን ጨምሮ ትምህርት ቤታችን እና ሌሎች ንብረቶቻችን ሲቃጠሉ መግለጽ የሚከብዱ ከባድ የተስፋ መቁረጥ ስሜቶች ተሰምተውኛል ብላናለች፡፡
በነዚህ ግጭቶች ምክንያት ህይወታችንን ለማትረፍ በተደጋጋሚ ለስደት ተዳርገናል የምትለው ተማሪ ገሊላ ሳይንቲስት የመሆን ምኞቴ ቀርቶ ፍላጎቴ በህይወት መኖር ብቻ እንደነበርም ተናግራለች፡።
በአጣዬ በደረሰው የጸጥታ ችግር ምክንያትም ለብዙ ወራት ትምህርት መቋረጡን ተከትሎ እና ቤት ንብረታችን በመቃጠሉ ምክንያት በወቅቱ የተሻለ ደህንነት ፍለጋ ወደ ሸዋሮቢት ከተማ መሰደዳቸውን አክላለች።
ከአንድ ዓመት በፊት ህወሓት ወደ ሰሜን ሸዋ ጥቃት በመክፈቱ ምክንያትም እሷ እና ቤተሰቦቿ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ደብረብርሃን መሰደዳቸውን ነግራናለች።
አካባቢው መልሶ ሲረጋጋ ግን ትምህርቷን ለመቀጠል ስትል በአንድ ዘመዷ እና በሸዋሮቢት ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እርዳታ ምክንያት ከ11ኛ ክፍል ሁለተኛ መንፈቀ- ትምህርት ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን እንደወሰደችም ነግራናለች።
ቤተሰቦቼ እና መምህራኖቼ ያደረጉልኝ ድጋፍ በጦርነቱ ምክንያት ያየኋቸውን መጥፎ ሁኔታዎች ሁሉ እንድረሳ አድርጎኛል የምትለው ተማሪ ገሊላ ቤተሰቦቿን እና መምህራንን አመስግናለች።
የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተናን በሰላም በደብረብርሃን ዩንቨርሲቲ ተፈትና 569 ማምጣቷን ጠቅሳለች። “መፈናቀሉ እና ጦርነቶቹ ሁሉ ባይኖሩ ከዚህ የተሻለ ውጤት ላመጣ እችል ነበር፣ ይሁንና ይህ ውጤት ወደ ዩንቨርሲቲ የሚያስገባኝ በመሆኑ አይከፋኝም” ብላለች። ይህ ውጤት ከሰሜን ሸዋ እና አካባቢው ከሴቶች ከፍተኛው ውጤት እንደሆነ ሰምተናል።
ጦርነት የሰውን ልጅ ሲገድል እና ድሃ ሲያደርግ አይቻለሁ ያለችን ተማሪ ገሊላ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ሰላምን ተመኝታለች።
በቀጣይ በዩንቨርሲቲ በሚኖራት ጊዜ ሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ማጥናት የመጀመሪያ ፍላጎቷ መሆኑን የነገረችን ተማሪ ገሊላ 12 ዓመት ሙሉ የለፉ የዘንድሮ ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤት በዚህ መልኩ መደምደሙ እንደሚያሳዝናትም ጠቁማለች።
የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት በሀገሪቱ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ1 ሺህ 161 መደበኛ ትምህርት ቤቶች አንድም ተፈታኝ ተማሪ ብሔራዊ ፈተናውን አላለፈም።
እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ካስፈተኑ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 798 ትምህርት ቤቶች ቢያንስ አንድ ተማሪ አሳልፈዋል ሲሉ ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።
በ2014 ዓ.ም በተሰጠው ፈተና በሁለቱም የትምህርት መስክ ፈተናውን ከወሰዱት 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ውስጥ 29 ሺህ 909 የሚሆኑት ተማሪዎች 50% እና በላይ ያስመዘገቡ ናቸውም ተብሏል።
ከፍተኛ ውጤት የተበዘገበበት የትምህርት መስክ በተፈጥሮ ሳይንስ 666 ከ700 ከፍተኛ ውጤት ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 524 ከ600 ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።