አዲሱ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሮያሊቲ ክፍያ ቀመር ምን ምን ይዟል?
የሮያሊቲ ክፍያ አለመጀመር አንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያዎች እና ቤተሰቦች በድህነት እንዲኖሩ አድርጓል ተብሏል
በአዲሱ መመሪያ መሰረት ሙዚቃን ተጠቅመው ገቢ እያገኙ ያሉ ሁሉም ተቋማት ክፍያ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ ተብሏል
አዲሱ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሮያሊቲ ክፍያ ቀመር ምን ምን ይዟል?
ኢትዮጵያ ከ1996 ዓ/ም ጀምሮ የአዕምሮ ፈጠራ ስራዎችን ጥቅም ለማስከበር ህግ ያወጣች ቢሆን በተለይም የሙዚቃ ባለሙያዎች ጥቅም ሳይከበር ቆይቷል፡፡
በ2007 ዓ/ም ደግሞ የአዕምሮ ስራ ውጤቶችን የበለጠ የሚያስከብር ነው የተባለ የተሻሻለ ህግ ያወጣች ቢሆንም ይህን ህግ መፈጸም እና መስፈጸም የሚያስችሉ መመሪያዎች ባለመውጣታቸው ምክንያት ህጉ እስካሁን መተግበር ሳይቻል ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅጂና ዘርፍ ማህበር የስራዎቻቸውን ጥቅም ለማስከበር ላለፉት 17 ዓመታት ሲታገል መቆየቱን አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት የሆኑት የሙዚቃ አቀናባሪው ዳዊት ይፍሩ ለአልዐይን እንዳሉት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለሙያዎች በለፉባቸው ስራዎቻቸው ሳይጠቀሙ ዲጄዎች ግን በአንድ ሁነት እስከ 100 ሺህ ብር እና ከዛ በላይ እየሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡
ራሳቸውን ለማዝናናት ብለው ሙዚቃዎችን በሚጠቀሙ ግለሰቦች ላይ ጥያቄ የለንም የሚሉት ፕሬዝዳንቱ ነገር ግን ለንግድ የተቋቋሙ ሚዲያዎች፣ መዝናኛ ቤቶች፣ ዲጄዎች እና የንግድ ተቋማት በነጻ የሚጠቀሙበት ወቅት ማለቁን ተናግረዋል፡፡
በስራዎቻቸው አንቱ የተባሉ ሙዚቀኞች እና ቤተሰቦቻቸው በድህነት ውስጥ እየኖሩ የነሱን ስራዎች እየተጠቀሙ ግን ሚሊየነር የሆኑ ተቋማት አሉ ያሉት የግጥም እና ዜማ ደራሲው ዳዊት ይፍሩ እነዚህ ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን ከተጠቀሙ ተቋማት ጥቅም ሊያገኙ የሚችሉባቸው የክፍያ ቀመር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ይህ የአዕምሮ ስራ ውጤቶች ክፍያ ቀመር ተጠቃሚ ተቋማትን እና ባለ መብቶችን በማይጎዳ፣ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መንገድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
ጎረቤት ሀገር ኬንያ የሮያሊቲ ክፍያ ከጀመሩ 15 ዓመታት አልፏቸዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ የክፍያ ቀመሩ የኬንያን፣ አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራትን ልምድ መነሻ በማድረግ በባለሙያዎች እንደተዘጋጀም ነግረውናል፡፡
የሮያሊቲ ክፍያ ረቂቅ መመሪያው የሚመለከታቸው አካላትን ባሳተፈ መንገድ እንደተዘጋጀ እና ህጉን ለማስፈጸም ስልጣን ለተሰጠው የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ማስገባታቸውንም ደራሲ ዳዊት አክለዋል፡፡
ክፍያ እንዲከፍሉ ከሚጠበቅባቸው ተቋማት መካከል ሚዲያዎች በመሆናቸው ከነሱ ክፍያ እንዴት ልትፈጽሙ አስባችኋል? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም “ የተወሰኑ የመንግስት ሚዲያዎች ሙዚቃዎችን የምናጫውተው ገቢ ለማግኘት ብለን አይደለም፣ ለህዝባዊ አገልግሎት ነው የሚሉ አስተያየቶችን አቅርበዋል፣ ይህ ግን ፈጽሞ ስህተት ነው፣ የአንጋፋ ሙዚቀኞችን ሙዚቃ እየተጠቀሙ የሙዚቃ ውድድሮችን ሳይቀር እያዘጋጁ፣ የአየር ሰዓቶችን እየሸጡ ከስፖንሰሮች ገቢ እየሰበሰቡ ለህዝብ ጥቅም ነው የምንሰራው ማለት ተቀባይነት የለውም“ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“በየምሽት መዝናኛ ቤቶች ሳይቀር የታዋቂ ሙዚቀኞችን ሙዚቃዎች በነጻ እየተጫወቱ እና እያጫወቱ ከፍተኛ ገቢ እየሰበሰቡ ያሉ ተቋማት ከሚያገኟት ገቢ ላይ ጥቂት ክፍያ በመክፈል ሙዚቀኞችን መደገፍ ይኖርባቸዋል” ያሉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ለዚህም ሁለት አይነት የክፍያ ቀመር መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
ሙዚቃ አጫዋቾች በምን መንገድ ነው ክፍያ እንዲከፍሏችሁ የምትፈልጉት? በሚል ላነሳነው ጥያቄም እኛ ባዘጋጀነው ረቂቅ የሮያሊቲ ክፍያ ቀመር መሰረት ሙዚቃ አጫዋቾች እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸው በአንድ ሙዚቃ እስከ 20 ሳንቲም ድረስ ነው፣ የክፍያ መንገዱም ለምሳሌ ሊያጫውቱት በሚችሉት የሙዚቃ መጠን ልክ ይሆናል፣ ከዓመታዊ ትርፋቸው ላይ እስከ 2 በመቶ፣ ክፍያቸውን ባጫወቱት ሙዚቃ ልክ አልያም የዓመት ፓኬጅ በመግዛት ሊሆንም ይችላል፣ እንደ ዲጄ እና መዝናኛ ቤቶች አይነት ደግሞ ከንግድ ፈቃዳቸው ጋር በማያያዝ እና በሚደረጉ ድርድሮች አማካኝነት ሊሆን ይችላል” ብለዋል፡፡
ዘንድሮ ከተለቀቁ የሙዚቃ አልበሞች የማንን ወደዱ?
ከሀገር ውስጥ የሙዚቃ አጫዋቾ እና ተጫዋቾች ተገቢውን የክፍያ አሰራር ከዘረጋን በኋላ ትኩረታችንን እንደ ስፖቲፋይ እና ዩቲዩብ አይነት ዓለም አቀፍ የሙዚቃ አጫዋች ተቋማት ጋር ድርድሮችን እንደሚያደርጉም የዜማ እና ግጥም ደራሲው ዳዊት ይፍሩ ተናግረዋል፡፡
ከነዚህ ተቋማት ጋር ከዚህ በፊት በተደረጉ የተወሰኑ ውይይቶች ወቅት ክፍያ የምትጠይቁን ከሆነ ሙዚቃዎቻችሁን አናጫውትም እያሉ ለማስፈራራት ሞክረዋል ያሉት ደራሲ ዳዊት ይህ ግን አይሰራም የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች በብዙ የዓለማችን ሀገራት የራሳቸው የሆኑ አድማጮች አሏቸው ላጫዋቷቸው ሙዚቃዎች ተገቢውን ክፍያ እንዲፈጽሙ ማድረጋችን የማይቀር ነውም ብለዋል፡፡