አዲሱ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ምን አዲስ ነገሮችን ይዟል?
ኢትዮጵያ አምስት አይነት ፓስፖርቶችን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጋለች

አዲሱ ፓስፖርት ለ10 ዓመት እንዲያገለግል ሆኖ መሰራቱ ተገልጿል
አዲሱ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ምን አዲስ ነገሮችን ይዟል?
የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አዲስ ፓስፖርቶችን ይፋ አድርጓል።
ዛሬ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ይፋ የተደረጉት ፓስፖርቶች አራት አይነት ሲሆኑ ከመደበኛ ፓስፖርት በተጨማሪ የዲፕሎማት፣ ውጭ ሀገራት እና የአገልግሎት ፓስፖርቶችም ይገኙበታል።
ፓስፖርቶቹ በጃፓኑ ቶፓን የደህንነት ኩባንያ እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ኩባንያ ትብብር ስለመመረቱም ተገልጿል።
10 ዓመት እንዲያገለግል ተደርጎ የተሰራው ይህ ፓስፖርት በአዲስ አበባ በሚገኘው ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የተመረተ ነው።
የፓስፖርቱ አገልግሎት ጊዜ 10 ዓመት መደረግ የዜጎችን ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበት እንደሚቆጥብ ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለም በፓስፖርቱ ውስጥ ገጾች ላይ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታዎች የሚያጎለብቱ እና ታሪካዊ ቅርጾችን ይዟልም ተብሏል።
እንዲሁም ፓስፖርቱ የማይክሮ ችፕስ የተገጠመለት መሆኑ ሀሰተኛ ፓስፖርቶችን በቀላሉ መለየት እንዲቻል ተደርጎ ስለመሰራቱም በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም ፓስፖርቱ የግለሰቡን መረጃና የጣት ዐሻራ የያዘ እንደሆነም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ካሉ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ተቋም ከተገልጋዮች ቅሬታ ከሚበዛበት መካከል አንዱ ነው።
ዜጎች ፓስፖርት በወቅቱ ካለማግኘታቸው ባለፈ ለህገወጥ ስደት፣ ገንዘብ ብዝበዛ እና ለሌሎች እንግልቶች እንደሚዳረጉ ሲናገሩ ይደመጣል።
አል ዐይን አማርኛ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ተከታታይ ዘገባዎችን ሲሰራ የቆየ ሲሆን ኢምግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት በበኩሉ ለፓስፖርት ፈላጊ ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት በየጊዜ ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግሯል።