በኢትዮጵያ የፓስፖርት ቀጠሮ ማስያዝ የሚችሉት ሌሊት ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ?
የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ድረገጽ ቀን ላይ መስራት አቁሟል
አዲስ የፓስፖርት አመልካቾች ፖስፖርታቸውን ከነሀሴ በፊት ማግኘት አይችሉም ተብሏል
የፓስፖርት ቀጠሮ ማስያዝ የሚችሉት ሌሊት ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ?
የፓስፖርት አገልግሎቶችን ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ድረገጹ የሚፈለገውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም።
የተቋሙን ድረገጽ በመጠቀም አዲስ ፖስፖርትም ሆነ ከፓስፖርት ጋር የተገናኙ ማለትም ፓስፖርት ማደስ እና ተያያዥ አገልግሎቶችን ለማግኘት ተገልጋዮች ወደ ድረገጹ ቢገቡም እየሰራላቸው እንዳልሆነ ሰምተናል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እና ቢሮ ተከራይተው ለተገልጋዮች ቀጠሮ በማስያዝ ስራ ላይ የተሰማሩ አንድ ግለሰብ እንደነገሩን ከሆነ "ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ቀን ቀን ላይ የተቋሙ ድረገጽ እየሰራ አይደለም" ብለዋል።
"ይህ ችግር ያጋጠመን ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ነው" ያሉን እኝህ አስተያየት ሰጪ " ድረገጹ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ድረስ ባሉት ጊዜያት አይሰራም" ብለውናል።
እያደረግን ያለነው የደንበኞቻችንን የልደት መረጃ እና መታወቂያን ተቀብለን ሌሊት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት እስከ ጠዋቱ አንድ ሰዓት ድረስ ብቻ እንቅልፋችንን ትተን እየሞላን ነው ሲሉም አክለዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ እና ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች አስተያየት ሰጪ ድርጅቱ ከፓስፖርት ጋር በተያያዘ በብቸኝነት አገልግሎት የሚሰጥበት ድረገጽ ላለፉት ቀናት ብሞክርም አይሰራም ብላናለች።
አስተያየት ሰጪዋ አክላም በቅርቡ ሰሜን አሜሪካ ካለው ባሏ ጋር ጋብቻ መፈጸሟን፣ ከባለቤቴ ጋር አብሬ ለመኖር እና ወደ ስፍራው ለመጓዝ ፖስፖርት ለማግኘት ማመልከት ብፈልግም ድረገጹ አልሰራላልኝም ስትል ገልጻለች።
ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለዚሁ አገልግሎት ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን የነገረን ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በበኩሉ አዲስ ፓስፖርት ለማግኘት የመጀመሪያ መስፈርት በድርጅቱ ድረገጽ ማመልከት እንዳለብኝ ተነግሮኝ ለማመልከት ብሞክርም ድረገጹ አልሰራልኝም ብሏል።
"በምኖርበት አካባቢ ብዙዎች ፓስፖርት ሲዘገይባቸው በህገወጥ መንገድ በባህር ወደ አረብ ሀገራት እየሄዱ ነው" የሚለው ይህ አስተያየት ሰጪ ህግን ተከትለን እንጓዝ ስንል ደግሞ ሁሉም ነገር ውስብስብ ይሆንብናል" ሲልም አክሏል።
"አዲስ አበባ የመጣሁት በመከላከያ ሰራዊት እና ፋኖ ውጊያ መሀል ነፍሴን አሲዤ ነበር" ያለው ይህ አስተያየት ሰጪ የፓስፖርት አገልግሎቱን ለማግኘት ያለው እንግልት "ተስፋ አስቆራጭ" ነው ሲል ተናግራል።
አልዐይን አማርኛ ባደረገው ተጨማሪ ማጣራት የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ድረገጽ ቢከፍትም በተለይም ቀን ላይ አዲስ ቀጠሮ ማስያዝ እና ማሳደስ አያስቻልም።
ከአዲስ ፓስፖርት ቀጠሮ መያዝ ውጪ ያሉት ፓስፖርት ማደስ እና መቀየር አገልግሎቶችን ለማግኘት ደግሞ ድረገጹ የተወሰነ ሂደት ይሄድና እንደሚቆምም አረጋግጠናል።
ሌሊት ላይ ብቻ ይሰራል የተባለውን ለማረጋገጥ ባደረግነው ሙከራ ንጋት ላይ ባሉ ሰዓታት ማለትም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እስከ አንድ ሰዓት ድረስ ድረገጹን በመጠቀም የፓስፖርት አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚቻል አረጋግጠናል።
አሁን ላይ አዲስ ፓስፖርት ለማግኘት የሚያስችሉ እንደ አሻራ እና ተጨማሪ የሰንድ ማስረጃዎችን መስጠት ከመስከረም በፊት እንደማይቻል ከድረገጹ ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
ጉዳዩን ይዘን ወደ ኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ያመራን ሲሆን የድርጅቱ ህዝብ ግንኙነት እና ኮሙንኬሽን ሀላፊ ወይዘሮ ማስታዋል ገዳ ድረገጹ ከአዲስ ፓስፖርት ማመልከት ውጪ ሌሎች አገልግሎቶች ሁሌም በስራ ላይ እንዳለ እና ያጋጠመ እክል እንደሌለ ተናግረዋል።
"አዲስ ፓስፖርት ለማግኘት ድረገጹ ሙሉ ለሙሉ እየሰራ ያልሆነው በየዕለቱ ተቋሙ ማስተናገድ ከሚችለው አቅም በላይ የሆኑ አመልካቾች በማመልከታቸው እንጂ የተወሰኑ አመልካቾችን እየተቀበለ እና እየተገለገሉ ነው" ሲሉም ሀላፊዋ ገልጸዋል።
ሀላፊዋ አክለውም ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የድርጅቱ የኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እየሰሩበት እንደሆነም ተናግረዋል።